ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየከፈተች ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየከፈተች እንደምትገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ እያካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

በማብራሪያቸውም የነገውን ዓለም አቀፋዊ ውድድር ለማሸነፍ የዛሬ ዝግጅት ወሳኝ መሆኑን ተናግረው፣ መንግሥት ወጣቶችን ለላቀ ስኬት ለማብቃት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከሀገሪቱ አምስት የዕድገት ምሰሶዎች መካከል አንዱ ቴክኖሎጂ እንዲሆን መደረጉ ለትውልድ የተሠራ ትልቅ ኢንቨስትመንት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ረገድ ኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየከፈተች መሆኗን አብራርተዋል።

በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በዓለም ሁለተኛ የሆነውን ግዙፍ የኤአይ (AI) ዩኒቨርሲቲ ለመገንባት በከፍተኛ ፍጥነት እየሠራች መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ታላቅ የትምህርት ተቋም በአንድ ዓመት ውስጥ ሥራ እንደሚጀምር ገልጸዋል።

አባቶቻችን የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና አየር ሀይልን ገንብተው በዓለም ስመጥር እንዳደረጉት ሁሉ፣ ይህ ዩኒቨርሲቲም ለኢትዮጵያ ልጆች የተሻለ ዘመንን እና ብሩህ የወደፊት ዕድልን ይዞ እንደሚመጣም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም