ቀጥታ፡

በመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከ34 ሺህ በላይ መዋዕለ ሕፃናት ተገንብተዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2018 (ኢዜአ)፦ በመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከ34 ሺህ በላይ መዋዕለ ሕፃናት መገንባታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ እያካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለሚቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው መንግስት በቀዳማይ የሕፃናት ትምህርት (Early Childhood Education) ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ይህም ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር ብሎም ነገን የዋጀ ትውልድ ለማዘጋጀት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ተናግረዋል። 

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከ34 ሺህ በላይ የመዋዕለ ሕፃናት መገንባታቸውን ጠቁመው በአሁኑ ወቅትም ከአራት ሚሊዮን በላይ ሕፃናት በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። 

ኢትዮጵያ ለአዳጊዎች እውቀት በሰጠችው ትኩረትም ነገን እየሰራች ትገኛለች ብለዋል፡፡  

የኢትዮጵያ የወደፊት ተስፋ ሕፃናት ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከልጅነታቸው ጀምረን ያስተማርናቸውና ያዘጋጀናቸው ሕጻናት በነገው ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉ ሲሉም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም