አርሰናል እና ቼልሲ በካራባኦ ዋንጫ የሚያደርጉት የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
አርሰናል እና ቼልሲ በካራባኦ ዋንጫ የሚያደርጉት የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ይጠበቃል
አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ካራባኦ ዋንጫ አርሰናል እና ቼልሲ ዛሬ በግማሽ ፍጻሜው የመልስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በኤምሬትስ ስታዲየም ይካሄዳል።
ጥር 6 ቀን 2018 ዓ.ም ቡድኖቹ ባደረጉት የግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታ አርሰናል 3 ለ 2 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
አርሰናል ሁለት ጊዜ የካራባኦ ዋንጫን አንስቷል። የሰሜን ለንደኑ ክለብ ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫውን ያነሳው እ.አ.አ 1992/93 ነው።
የለንደን ጎረቤቱ ቼልሲ የካራባኦ ዋንጫ ውድድርን አምስት ጊዜ አሸንፏል። እ.አ.አ በ2015 ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫውን ያነሳበት ወቅት ነበር።
ቡድኖቹ በካራባኦ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለአምስኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም እርስ በእርስ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች አርሰናል ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናው ቼልሲ አንድ ጊዜ አሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
በዛሬው ጨዋታ ባለሜዳው አርሰናል ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ለፍጻሜ ያሳልፈዋል።
ተጋጣሚው ቼልሲ ከሁለት እና ከዛ በላይ የግብ ልዩነት ካሸነፈ ለፍጻሜ ማለፉን ያረጋግጣል።
የምዕራብ ለንደኑ ክለብ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1 ለ 0 ቢያሸነፍ በድምር ውጤት ቡድኖቹ ሶስት አቻ ስለሚሆኑ ጨዋታው ወደ ጭማሬ ሰዓት ያመራል።
በካራባኦ ዋንጫ ከሜዳው ውጪ ብዙ ጎል ያገባ የሚለው ህግ ተግባራዊ አይሆንም።
የ43 ዓመቱ ፒተር ባንክስ ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
የጨዋታው አሸናፊ በፍጻሜው ከማንችስተር ሲቲ እና ኒውካስትል ዩናይትድ አሸናፊ በፍጻሜ ይገናኛል።
እ.አ.አ በ1960 የተጀመረው የካራባኦ ካፕ (በቀድሞ አጠራሩ የእንግሊዝ ፉትቦል ሊግ ዋንጫ) በእንግሊዝ ከአንጋፋው ኤፍ ካፕ ውጪ የሚደረገው የጥሎ ማለፍ ውድድር ነው።
ሊቨርፑል 10 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የውድድሩ ስኬታማ ክለብ ነው። ማንችስተር ሲቲ ስምንት እና ማንችስተር ዩናይትድ ስድስት ጊዜ ውድድሩን በማሸነፍ ይከተላሉ።