ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የቡና ምርታማነት የፖሊሲ እርምጃ ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር ምሳሌ የሚሆን ተጨባጭ ውጤት አስገኝቷል 

አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የቡና ምርታማነት የፖሊሲ እርምጃ ለአፍሪካ ቡና አምራች ሀገራት ጭምር ምሳሌ የሚሆን ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን የግብርና ሚኒስትር ደኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) አስታወቁ።

ዛሬን ጨምሮ ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የሚቆየው የአፍሪካ የቡና ሳምንት ከፍተኛ የፖሊሲ ፎረም የአህጉሪቷ ቡና አምራች ሀገራት፣ የልማት አጋሮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።


 

የአፍሪካ ቡና ሳምንት ከፍተኛ የፖሊሲ ፎረሙ የቡና ዕሴት ሰንሰለት ተግዳሮቶችን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማመላከት የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም የቡና ምርታማነት ሥርዓትን ለማሻሻል ያለመ ነው።  

በዚሁ ወቅት የግብርና ሚኒስትር ደኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የቡና ምርታማነትን ለማሻሻል የወሰደቻቸው የፖሊሲ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት አስገኝተዋል ብለዋል።

በዚህም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ ለቡና አምራች አርሶ አደሮችና ላኪዎች የሚደረግ ድጋፍና ክትትል የቡና ምርታማነትና የገቢ አቅምን በማሳደግ ለአፍሪካ ቡና አምራች ሀገራት ጭምር ምሳሌ የሚሆን ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን አስታውቀዋል።

የአፍሪካ ቡና አምራች ሀገራትም ዕሴት የታከለበትና ያለቀለት የቡና ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ውጤታማ ትብብርና ተግባራዊ እርምጃን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።


 

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት የሚፈጥራቸውን ገበያዎች በመጠቀም የአህጉሪቷን የቡና ምርት ጥራትና የገበያ ተደራሽነትን በማስፋት የጋራ ተጠቃሚነት ዕድሎችን ማጎልበት ያስፈልጋል ብለዋል።

በቀጣይም የአፍሪካን የቡና ምርት ተጠቃሚነት ለማሻሻል የዓለም ገበያ የሚፈልገውን ደረጃ ማሟላት የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ተወካይ አምባሳደር ሞሀመድ አል አሚን ሱፍ፤ የአፍሪካን የቡና ምርታማነት ለማሻሻል የመንግሥትና የግል አጋርነት ኢንቨስትመንትን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።


 

በዚህም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የሚቋቋም የቡና ልማትን ማዕከል በማድረግ አፍሪካ ዕሴት የታከለበት የቡና ምርት ለዓለም ገበያ እንድታቀርብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመንግሥታቱ ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ተወካይ ስቴፌን ካርግቦ በበኩላቸው፤ የአፍሪካን የቡና አምራቾችና አቀነባባሪዎች አቅም የሚያሳድግ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በቀጣይም የአፍሪካ ሀገራት ቡና አምራች አርሶ አደሮች የሚያጋጥማቸውን ጫና መቋቋም የሚያስችል ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ዑመር በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የቡና ልማትና ምርታማነትን ማሻሻል የሚያስችል አቅምና ተሞክሮ ገንብታለች ብለዋል።


 

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ተግባራዊ የተደረገው የአረንጓዴ አሻራ  መርሃ ግብር በቡና ልማት ውጤታማነት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

የአፍሪካ የቡና ሳምንትም ኢትዮጵያ በቡና ምርታማነት ያመጣችውን እመርታዊ ለውጥ ለአህጉሪቷ ቡና አምራች ሀገራት በማስተዋወቅና የገበያ አማራጮችን ለማስፋት ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም