የኢትዮጵያ አቪዬሽን ደህንነት የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የአቪዬሽን ዘርፉን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት የሚያጠናክር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አቪዬሽን ደህንነት የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የአቪዬሽን ዘርፉን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት የሚያጠናክር ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ደህንነት የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የአቪዬሽን ዘርፉን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና ተቀባይነት የሚያጠናክር መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 14/2018 ዓ.ም በ9ኛ መደበኛ ስብሰባው ሶስት የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መምራቱ ይታወቃል።
በእለቱም የኢትዮጵያ አቪዬሽን ደህንነት አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ምክር ቤቱ ለዝርዝር ዕይታ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
በዚህም ቋሚ ኮሚቴው ረቂቅ አዋጁን መርምሮ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ ለማቅረብ እንዲችል በዛሬው ዕለት የአስረጂ መድረክ አካሂዷል።
በዚህ ወቅት በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሕግ ዳይሬክተር አማረ ኢቲቻ፤ አቪዬሽን ዘርፍ የድህንነት ስጋት በየጊዜው ተለዋዋጭና ውስብስብ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
የአቪዬሽን ደኅንነት ስጋቶች በአስተማማኝ አቅም ለመመከት ለ21 ዓመታት ያገለገለውን የኢትዮጵያ አቪዬሽን ሴኩሪቲ አዋጅ ቁጥር 432/1997 ከዓለም አቀፍ አሰራር ጋር በማጣጣም ማሻሻል አስፈልጓል ብለዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላትም የአቪዬሽን ደህንነት አዋጅ ቁጥር 432/1997 ለማሻሻል መነሻ የሆኑ ምክንያቶችንና የባለድርሻ አካላትን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ምላሽና ማብራሪያዎችን ጠይቀዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ርስቱ ይርዳው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተመራጭ ካደረጉት ዋነኛ ጉዳዮች አንዱ የአቪዬሽን አስተማማኝ ደህንነት መሆኑን ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት መስፈርት የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተመራጭነት በማስቀጠል የደኅንነት ዘላቂነትን ለማስጠበቅ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።
በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ደኅንነት ዳይሬክተር አስራት ቀጄላ፤ ረቂቅ አዋጁ አቪዬሽን ደህንነት የአገልግሎት ክፍያ ደኅንነትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።
የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ደኅንነት አስተማማኝነት በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ዕውቅናን ያገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
ረቂቅ አዋጁም የአቪዬሽን ደኅንነትን የመፈፀም አቅም የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ መህዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ የአቪዬሽን ደኅንነት አስተማማኝነትን በማጠናከር የዘርፉን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና ተቀባይነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።