በጀትን በአግባቡ ስራ ላይ በማዋል የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጀትን በአግባቡ ስራ ላይ በማዋል የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባራት ይጠናከራሉ
ወላይታ ሶዶ፤ ጥር 25/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት በጀትን በአግባቡ ስራ ላይ በማዋል የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕላን ቢሮ የ2018 በጀት አመት የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማና በቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የሴክተር ምክክር ጉባኤ በወላይታ ሶዶ ከተማ አካሂዷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ተፈሪ አባተ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የመንግስት ሃብትን በአግባቡ ስራ ላይ በማዋል የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ ነው፡፡
ለዚህም ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ቢሮው ድጋፍና ክትትሉን ማጠናከሩን አንስተዋል፡፡
የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍቃደስላስ ቤዛ በበኩላቸው፤ ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ዘላቂ ልማትን እውን በማድረግ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ፕሮጀክቶች በእቅድ መመራታቸውን ተናግረዋል፡፡
የክልሉን ሀብት የመለየትና የመንገድ ተደራሽነትን የሚያሳይ ጥናት ተጠናቅቆ ዲጂታላይዝ የማድረግ ስራ መሰራቱንም አመልክተዋል።
የመንግስትን ሀብት በአግባቡ ስራ ላይ ለማዋል የባለድርሻ አካላት ቅንጅትን ማጠናከር ላይ ትኩረት መሰጠቱንም አመልክተዋል።
የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ቦጋለ ቦሼ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የፕላንና ልማት ቢሮ ከተለመደው አሰራር በመውጣት በውጤት የሚለካ ዕቅድ ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም የመንግስትን ሀብት ያማከለና የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው የ2030 ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
በምክክር ጉባኤው የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።