በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ ልማት ላይ ለማዋል ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ ልማት ላይ ለማዋል ትኩረት ተሰጥቷል
ባህር ዳር ፤ ጥር 25/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ በመሰብሰብ ልማት ላይ ለማዋል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ገለፀ።
የቢሮው የገቢ ትምህርትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ታዘባቸው ጣሴ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።
እቅዱን ለማሳካትም አገልግሎቱን ማዘመንና የአመራርና የባለሙያ ቅንጅትን ማጠናከር ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።
አገልግሎቱን ለማዘመን ተግባራዊ የተደረገው የኤሌክትሮኒክስ ታክስ አስተዳደር ስርዓት ግብር ከፋዮች ባሉበት ቦታ ሆነው ግብራቸውን በመክፈል ጊዜንና አላስፈላጊ ወጪያቸውን እንዲቀንሱ ከማስቻል ባለፈ የሚሰበሰበው ገቢ እንዲያድግ እያገዘ መሆኑን አመልክተዋል።
ቴክኖሎጂውን በክልሉ ካሉ 257 የታክስ ማዕከላት ውስጥ በ225ቱ ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል ።
በዚህም በሚሰበሰበው ገቢ ልማትን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በክልሉ በበጀት አመቱ እስከ ጥር 22 ቀን 2018 ዓም ድረስ 45 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።
የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በ15 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ጭማሬ እንዳለው አመልክተዋል።
የገቢ አሰባሰቡ ማደግም የክልሉን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በተሻለ ደረጃ ለመፍታት እያገዘ መሆኑን አብራርተዋል።
በዘርፉ የህግ ተገዥነትን ለማስረፅ ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር ደረሰኝ ሳይቆርጡ ግብይት ሲፈፅሙ የተገኙ 797 ግብር ከፋይ ነጋዴዎች በገንዘብ መቀጣታቸውንም ተናግረዋል።
እንዲሁም በግብር አሰባሰብ ሂደቱ ከአሰራር ውጭ ሲንቀሳቀሱ በተገኙ 133 የገቢ ተቋሙ ሰራተኞች ላይ ከቀላል እስከ ስራ ስንብት የደረሰ የዲሲፕሊን እርምጃ መወሰዱን አመልክተዋል።
በቀጣይ ወራትም ዕቅዱን በተሟላ መንገድ ለማሳካት በተሻለ ቅንጅትና ተነሳሽነት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።