ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢ-ተገማችና ተለዋዋጭ የዓለም ሁኔታ ውስጥ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል

አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በኢ-ተገማችና ተለዋዋጭ የዓለም ሁኔታ ውስጥ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ተጠሪ ተቋማትን የ2018 በጀት አመት የስድስት ወር ዕቅድ አፈፃፀም ገምግሟል።


 

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የባንኩንና የተጠሪ ተቋማትን ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረቡበት ወቅት፤ ብሔራዊ ባንክ የኢትዮጵያ የገንዘብና የፋይናንስ ሥርዓት ታማኝ ጠባቂ ነው ብለዋል።

በዚህም የዓለም ኢኮኖሚ ባልተረጋጋበት ሁኔታ ውስጥ የዋጋ ግሽበትን አምና ከነበረበት 17 በመቶ አሁን ላይ ወደ 9 ነጥብ 7 በመቶ የነጠላ አሀዝ በማውረድ ስኬታማ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

የመንግሥት የበጀት ጉድለት ከግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ እንዲሸፈን መደረጉና የብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ አጠቃቀም ፖሊሲ ትግበራ ለዋጋ ግሽበቱ ወደ ነጠላ አሀዝ መውረድ አዎንታዊ ሚና መጫወታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ጨምሮ ባንኮች 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገንዘብ በማሰባሰብ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ33 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገባቸውን አስረድተዋል።

በመደበኛውና በትይዩ ገበያ መካከል ያለውን የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት ከፍተኛ ደረጃ መጥበቡን የገለጹት ዶክተር ኢዮብ፥ የባንክ ዘርፍ ተቀማጭ ገንዘብ ክምችት 4 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር መድረሱን አስገንዝበዋል።

ይህም የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በኢ-ተገማችና ተለዋዋጭ የዓለም ሁኔታ ውስጥ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን እንደሚያሳይ አብራርተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በብዙ አመላካቾች ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው፥ የወጪ ንግድ ገቢን ከ3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የባንኮችን የተበላሸ የብድር መጠን ከ5 በመቶ እንዳይበልጥ በተከናወኑ ተግባራት በስድስት ወራት ውስጥ የባንኮችን የተበላሸ ብድር ማስተካከል የሚያስችል አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትርፋማ፣ ጤናማና በቂ የካፒታል አቅም ያላቸው የፋይናንስ ተቋማትን መፍጠር ያስቻሉ ተግባራዊ ውጤቶች መመዝገባቸውንም አንስተዋል።


 

የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ በበኩላቸው፤ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ በመከተል የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አኃዝ ዝቅ ማድረጉ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውም በፋይናንስ ዘርፍ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን መፍትሔ መስጠት ያስቻሉ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ለማሻሻል የተከናወኑ አበረታች ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም