የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከላት የዜጎችን የመንግስት አገልግሎቶች የጥራት ፍላጎት እያስጠበቁ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከላት የዜጎችን የመንግስት አገልግሎቶች የጥራት ፍላጎት እያስጠበቁ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2018(ኢዜአ)፦የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከላት የዜጎችን የመንግስት አገልግሎቶች የጥራት ፍላጎት እያስጠበቁ መሆናቸውን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አልማዝ መሰለ ገለፁ።
የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ምክትል ኮሚሽነር አልማዝ መሰለ እንደተናገሩት፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በፖሊሲ፣ በሪፎርምና በሕግ ማዕቀፍ በተቀመጠ አቅጣጫ መነሻነት የተተገበረ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመንግስትን አገልግሎት ማሳለጥ እንደሚያስፈልግ በሰጡት ልዩ ትኩረት መነሻነት ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም በመጀመሪያው ምዕራፍ በፌዴራል የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በ12 ተቋማትና በ41 አገልግሎቶች ተግባራዊ ማድረግ እንደተጀመረ አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም የፌደራል የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ወደ 23 በማሳደግ አጠቃላይ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ወደ 180 በማሳደግ ህዝቡ እንዲገለገል እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽነትን ወደታችኛው የመንግስት መዋቅር በማስፋት በክልሎች ጭምር ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በፌደራልና በክልሎች እየተስፋፋ የመጣው የመሶብ አንድ ማዕከላት አገልግሎትም የህብረተሰቡን የአገልግሎት ጥራት ፍላጎት በማሻሻል አዎንታዊ ሚና እየተወጡ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ለመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሰጪ ሙያተኞችም ተገቢውን ስልጠና በመስጠት ለተገልጋዮች ጥራት ያለው የመንግስት አገልግሎት እንዲያቀርቡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም በከንቲባ የሚመሩ ከተሞች አገልግሎታቸውን በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲሰጡ በማስቻል ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።