ቀጥታ፡

በግማሽ ዓመቱ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል

አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2018(ኢዜአ)፦ በ2018 በጀት አመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ ገለፁ፡፡

ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የውጭ ባለሃብቶችን በመሳብ ረገድ አበረታች ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ26 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመላክተዋል፡፡

በግማሽ ዓመቱ 245 የውጭ ባለሀብቶች አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ስኬቶች ኢትዮጵያን በአፍሪካ ሁለተኛ በምስራቅ አፍሪካ ደግሞ አንደኛ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ተቀባይ አገር እንዳደረጓት ተናግረዋል፡፡

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው እና መንግስት ከግል ባለሃብቶች ጋር የሚያደርጋቸው ተከታታይ ውይይቶች ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡

ፈጣን የመንግስት አገልግሎት እና የመሰረተ ልማት መስፋፋት ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሌሎች ዘርፎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና ዲጂታላይዜሽን ፈጣንና ጥራት ያላቸው አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ማደግ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም እንዲሁ፡፡

የንግድ ዘርፉ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት መደረጉም ትላልቅ ኩባንያዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እያደረገ ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ባለፉት ስድስት ወራትም 37 የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ ፈቃድ መውሰዳቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም