በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ሁሉም የመንግስት አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ይገባሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ሁሉም የመንግስት አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ይገባሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2018(ኢዜአ)፦በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ሁሉም የመንግስት አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንደሚገቡ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለም ፀሐይ ጳውሎስ ገለጹ።
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆኑ አስፈጻሚ ተቋማት የ2018 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ተገምግሟል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለም ፀሐይ ጳውሎስ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ለዜጎች የተቀላጠፈ እና ከብልሹ አሰራር የጸዳ አገልግሎት ለመስጠት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሚናው የጎላ ነው።
ይህንንም እውን ለማድረግ በፌደራል ተቋማት የሚሰጡ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የማስገባት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁንም አገልግሎቶችን ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስርዓት ከማስገባት አንጻር ውስንነቶች መኖራቸውን ገልጸው፤ ይህን ለመቅረፍ በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ሁሉም የመንግስት አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲካተቱ ይደረጋል ብለዋል።
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በኦንላይን መሰጠት የሚገባቸውን አገልግሎቶች በኦንላይን እንዲሁም በአካል መሰጠት ያለባቸውን አገልግሎቶች በማእከሉ መስጠት የሚቻልበትን አቅም መፍጠር አለብንም ብለዋል።
እቅዱም እውን እንዲሆን የሚመለከታቸው ተቋማት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አመላክተዋል።