ቀጥታ፡

የንጽህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክቱ ጥያቄያችንን መልሷል-ነዋሪዎች

ገንዳውኃ፤ ጥር 25/2018(ኢዜአ)፦በምዕራብ ጎንደር ዞን አርማጭሆ ወረዳ የተገነባው የንጽህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በተደጋጋሚ ሲያነሱት  የነበረውን ጥያቄ የመለሰና እንግልትን ያስቀረ መሆኑን   ነዋሪዎች ገለጹ ።

በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ከ108 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

የፕሮጀክቱን ወደ ሥራ መግባት ተከትሎ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች በአካበቢው የመጠጥ ውሃ ችግር እንደነበር አስታውሰዋል።

ፕሮጀክቱ በተደጋጋሚ ሲያነሱት የነበረውን የውሃ ጥያቄ የመለሰና  ውሃ ፍለጋ የነበረባቸውን እንግልት ያስቀረ መሆኑን ተናግረዋል።

የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የጋብላ ከተማ ነዋሪ ማለደ መካሻው እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱ የከተማዋን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦች ችግር ያቃልላል።


 

ቀደም ሲል ውሃ ፍለጋ ያጠፉት ከነበረው ጊዜና እንግልት ባለፈ ንጽህናው ባልተጠበቀ ውሃ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ብርቱካን ላመስግነው በበኩላቸው፤ በከተማዋ በነበረው የውሃ እጥረት የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን በአግባቡ መከወን እንዳይችሉ ማድረጉን አመልክተዋል።

የውሃ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱ  ቀደም ሲል ውሃ ፍለጋ ያጠፉት የነበረውን ጊዜና ጉልበት ያስቀረ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የውሃና ኢነርጂ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መለሰ ታከለ እንደገለጹት፤ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ነዋሪ ተደጋጋሚ ጥያቄ የሚመልስና የውሃ ፍላጎት የሚያሟላ ነው። 

ከ108 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት 200ሜትር ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ የተደረገለት መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ 3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ 500 ሺህ ሊትር የውሃ ማጠራቀሚያ እንዲሁም 20 የውሃ ማከፋፈያ ቦኖ ማካተቱንም አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ታዳጊዋን የጋብላ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ከነበረበት 53 በመቶ ወደ 78 በመቶ የሚያሳድግ መሆኑንም አብራርተዋል።


 

በምዕራብ ጎንደር ዞን ውሃና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ ተወካይ ግርማ ሽመላሽ በበኩላቸው፣በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ሁለት ጥልቅ ጉድጓዶችና 12 መለስተኛ የእጅ ጉድጓድ ፕሮጀክቶች ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በቅርቡ በ280 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የሰባት ጥልቅ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ግንባታ በማስጀመር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም