ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ማሳካት  መለያው ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2018(ኢዜአ)፦የመደመር መንግሥት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ማሳካት መለያው መሆኑን በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ያከናወናቸው ተግባራት አሳይተዋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆኑ አስፈጻሚ ተቋማት የ2018 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ተገምግሟል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የብልፅግና ዕሳቤ መሬት ነክቶ ፍሬ እያፈራ መሆኑን በማንሳት፥ ለዚህ ደግሞ ተቋማትና የተቋማት መሪዎች ግንባር ቀደም ተዋንያን ናቸው ብለዋል፡፡

የብልፅግና ጉዞ የሚታይና የሚዳሰስ ሥራና ውጤትን የሚፈልግ መሆኑን በመግለጽ፥ በዚህ ረገድ ተጨባጭ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

በ2018 ዓ.ም የአዲስ ዓመት ዋዜማ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ መመረቁን በማውሳት፥ በወቅቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ የሆኑ የጉባ ታላላቅ ብስራቶችም ወደ ትግበራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲሁም የነዳጅ እና የማዳበሪያ ፋብሪካን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጀምረናል ነው ያሉት። 

መንግሥታችን ጀምሮ በፍጥነት መጨረስ መለያው ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ ተቋማትም አርዓያነት ያለው ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የተጠሪ ተቋማት አመራሮች በበኩላቸው፥ በየዘርፋቸው በግማሽ ዓመቱ ያቀዱትን ተግባር በማሳካት በኩል በርካታ ሥራዎችን መተግበራቸውን አንስተዋል። 


 

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረ፤ የፋይናንስ ስርዓቱና የግብይት ሂደቱ ከወንጀል የጸዳ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ከፍተኛ ለውጥ እየመጣ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ፥ በግማሽ ዓመቱ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ26 በመቶ ዕድገት ያለው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳቡን ጠቅሰዋል።


 

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው፣ ኢላማ ተኮር የኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ ሥራ፣ ዲጂታል አገልግሎትና አዳዲስ ዘርፎችን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት መደረጉ ለተገኘው ውጤት ሚናቸው የላቀ ነው ብለዋል።

ሁሉም ተቋማት በሪፎርም ውስጥ መሆናችውን በመግለጽ፤ በሪፎርሞቻቸው የተሟላ አጀንዳ በመያዝ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ጨምሮ በአገልግሎት አሰጣጣቸው በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል ያሉት ደግሞ የኢሜግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጎሳ ደምሴ ናቸው።  


 

የመንግሥት አገልግሎትን ማዘመን አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ያነሱት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አልማዝ መሠለ በበኩላቸው፥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኒሼቲቭ እውን የሆነው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በርካታ ለውጦችን እያመጣ  መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለም ፀሐይ ጳውሎስ፥  ባለፉት ስድስት ወራት የተመዘገቡ ስኬቶች አበረታች መሆናቸውን በማንሳት  ለቀጣይ የላቀ ውጤት መትጋት ይገባል ብለዋል።


 

ለዚህም ሁሉም ተቋማት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን፣ የፋይዳ መታወቂያን፣ የ5 ሚሊዮን ኮደረስ ኢኒሼቲቭን ለማሳካት በተቀናጀ መንገድ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

አገልግሎት አሰጣጥን  ወደ ዲጂታል ማሸጋገርና ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማስገባትም ከሁሉም ተቋማት እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በሰጡት ማጠቃለያ፥  የሀገርን የዕድገትና የልማት ጉዞ የሚመጥን ዝግጁነትና ተግባር ከሁሉም ተቋማት እንደሚጠበቅ አፅንኦት ሰጥተዋል።


 

ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ አገልግሎትን በማቀላጠፍ፣ በገቢ አሰባሰብና በሌሎችም ዘርፎች የተገኙ መልካም ውጤቶች የሚያዘናጉ ሳይሆኑ የላቀ አቅዶ ለመፈጸም መነሻ መሆን አለባቸው ብለዋል።

ለዚህም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ ተቋማት እያንዳንዱ የሚያከናውኑት ሥራ ከአንድ ተቋም ያለፈና የኢትዮጵያን ከፍታ የሚገልፅ መሆን አለበት ነው ያሉት።

እነዚህ ተቋማት ለሌሎች አካላት ምሳሌ የሚሆን ተግባርና ውጤት እንደሚጠበቅባቸው በማንሳት፥ ኢትዮጵያን  በውጤት ለሌሎች ሀገራት ምርጥ ምሳሌ ለማድረግ መረባረብ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም