ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ፈጣን የስኬት ጉዞ የአፍሪካ የከተሜነት ውበት መገለጫ እያደረጋት ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2018(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ፈጣን የስኬት ጉዞ የኢትዮጵያ ከተሞች የብልጽግና ተምሳሌት እና የአፍሪካ የከተሜነት ውበት መገለጫ እያደረጋት መሆኑን የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በአዲስ አበባ በአጭር ጊዜ የተገነቡ የኮሪደር፣ የወንዝ ዳርና ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች ዘመናዊ ከተሜነትን የገለጡ ሆነዋል።


 

በአዲስ አበባ ተሰናስለው የተገነቡ መሠረተ ልማቶችም ጎስቋላ ገጽታን በዘመናዊ የከተሜነት የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ለነዋሪዎችና ጎብኝዎች ምቹ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ምኅዳርን ፈጥሯል።

የአፍሪካ ሕብረት፣ የበርካታ ሀገራት ኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንዲሁም የቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች የስበት ማዕከል በመሆን ከፍተኛ አድናቆት እየተቸራት ይገኛል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስደማሚ የዘመናዊ ከተሜነት የልማት ስኬትም የበርካታ ሀገራት መሪዎችና የከተማ ልማት ሙያተኞች በሀገራቸው ለመድገም ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ መጥተዋል።


 

የዘንድሮው 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ለአባል ሀገራት ተሳታፊዎችም የአዲስ አበባን የልማት ተሞክሮ ለመቅሰም መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች፤ በአዲስ አበባ በየቀኑ የሚታዩ አስደማሚ የልማት ውጤቶች ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ከተሞች ጭምር የውበት ተምሳሌት እያደረጋት መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪዋ ፍቅር አንለይ፤ ለነዋሪዎችና ጉብኝዎች ምቹ ምኅዳርን የፈጠሩ አስደናቂ የልማት ስኬቶች የኢትዮጵያን የመፈጸም አቅም ምሳሌነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልፃለች።


 

የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የአባል ሀገራት ተሳታፊ እንግዶችም የመዲናዋን የዕድገት ጉዞ በማየት የኢትዮጵያን ፈጣን የልማት ግስጋሴ የሚረዱበትን ዕድል ይፈጥራል ብላለች።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ መስፍን ከተማ በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ ፈጣን የለውጥ መንገድ ለነዋሪዎች ምቹ የከተሜነት ዘይቤ በመፍጠር ለሌሎች ከተሞችም በተሞክሮነት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

አዲስ አበባን የሚጎበኙ እንግዶችም በኮሪደርና በወንዝ ዳርቻ ልማት ከተገኙ ስኬቶች ልምድና ተሞክሮ የሚቀስሙበት ዕድል መኖሩን ተናግረዋል።

የመዲናዋ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስኬቶች የኢትዮጵያን ትክክለኛ የዕድገት ጉዞና ገጽታ በመግለጥ ለነዋሪዎችና ጉብኝዎቿ ምቹ ምኅዳርን የፈጠሩ ናቸው ያለው ደግሞ እስራኤል አበራ ነው።


 

የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ የሚኖራቸው ቆይታም መዲናዋ የአፍሪካዊያን ማዕከል እንደሆነች በተግባር የሚያረጋግጡበት እንደሚሆን ገልጿል። 

ቅድመ አያቶች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የተጎናጸፉትን የነፃነት የድል ታሪክ የአሁኑ ትውልድ በልማት አርበኝነት ለአፍሪካዊያን የሚያስተምርበት ጉዞ ላይ መሆኑን አንስቷል።


 

በመዲናዋ መናፈሻ ስፍራዎች ያገኘናቸው  ዘሚካኤል በላይ በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ የልማት ስኬቶች የነዋሪዎችን ማህበራዊ መስተጋብር የሚያጋምዱ ናቸው ብለዋል።

የአዲስ አበባ የኮሪደርና ሁለንተናዊ የልማት ለውጦች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሻሻል የሚያስችሉ  መሆናቸውን ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም