በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ የልማት ተግባራት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት አሳድገዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ የልማት ተግባራት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት አሳድገዋል
ወልቂጤ ፤ ጥር 25/2018(ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የህዝብን ተጠቃሚነት ያሳደጉ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ።
የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባዔ በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው የስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ የልማት ተግባራት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት አሳድገዋል።
የልማት ስራዎቹ የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡና የልማት አቅሞችን ወደ ውጤት ለመቀየር በተደረገው ጥረት የተከናወኑ መሆናቸውን አክለዋል።
የግብርናውን ዘርፍ አቅም ለመጠቀም ለአዝርዕትና ሆርቲካልቸር እንዲሁም ለበጋ መስኖ ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ጠቅሰው በግብዓት አቅርቦት እና አሲዳማ አፈር በኖራ በማከም ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን አንስተዋል።
በዚህም ከ459 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳን በተለያዩ ሰብሎች በማልማት ከ63 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱንም ጠቅሰዋል።
በክልሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የቅመማ ቅመም ምርት ላይ ትኩረት በመሰጠቱ ከ2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን አንስተዋል።
ሰው ተኮር ስራዎችን በመተግበር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የአርሶ አደሩን የገቢ አቅም ማሳደግ እንደተቻለም ተናግረዋል።
የኑሮ ውድነት ተፅዕኖን ለመቋቋምና ገበያን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ስራዎችን በቅንጅት በመስራት ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው ለዚህም በክልሉ 176 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን በማደራጀት አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በክልሉ ሰባት ከተሞች የአገልግሎት መስጫ የቢሮ ግንባታዎችን ጨምሮ ሌሎች የመንገድ እና የውሃ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ጀምሮ በመጨረስ ውጤታማ ተግባራት እያከናወኑ መሆናቸውን ነው ያረጋገጡት።
በክልሉ አስተናጋጅነት 20ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በተሳካ ሁኔታ እንዲከበር ግዙፍ መሰረተ ልማቶችን በወራት ገንብቶ በማጠናቀቅ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አሳይተናል ብለዋል።
በመተጋገዝ እና በጋራ ርብርብ ክልሉን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማሻገር እየተከናወነ ያለው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።