የሌማት ትሩፋት ከራስ ፍጆታ ባለፈ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን አሳድጓል - ኢዜአ አማርኛ
የሌማት ትሩፋት ከራስ ፍጆታ ባለፈ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን አሳድጓል
ደሴ ፤ ጥር 25/2018(ኢዜአ)፦ የሌማት ትሩፋት ከራስ ፍጆታ ባለፈ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እንዳሳደገላቸው የሐይቅ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል በምታደርገው ጥረት ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በተለያዩ አካባቢዎች በግልና በቡድን እየተተገበረ ያለው የሌማት ትሩፋት ከራስ ፍጆታ አልፎ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በብዛትና በጥራት ማምረት አስችሏል።
በመርሃ-ግብሩ የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ጨምሮ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ሁሉም ዜጋ ባለው ቦታ ላይ ምግቡን የሚያመርትበት ብሎም ለገበያ የሚያቀርብበት ዕድል ተፈጥሯል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የሐይቅ ከተማ የሌማት ትሩፋት ተጠቃሚዎችም በመርሃ-ግብሩ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ነው ያረጋገጡት።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ሻምበል ሀብቴ፣ ከአራት ጓደኞቹ ጋር ተደራጅቶ በተመቻቸላቸው የመሥሪያ ቦታ በዶሮ እርባታ መሰማራቱን ይናገራል።
በወቅቱ በ200ሺ ብር ካፒታል የ45 ቀን ጫጩት በማሳደግ የስጋና እንቁላል ጣይ ዶሮ በማርባት የጀመሩት ሥራ አሁን የዶሮዎቹ ብዛት ከሁለት ሺ መዝለሉንና ካፒታላቸውም ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱን አመልክቷል።
በመርሃ-ግብሩ ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንና ከገቢያቸው ላይ በመቆጠብም ዘመናዊ ሼድ ለመገንባት ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል ብሏል።
በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን በመጠቀም የወተት ምርታቸው መጨመሩን የሚናገሩት ደግሞ ሀሊማ አህመድ ናቸው።
ከስድስት የወተት ላሞች በቀን ከ50 ሊትር በላይ ወተት በማምረት ለሆቴሎች፣ ለካፌዎችና ለግል ተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በተመቻቸላቸው የባለሙያና የሼድ አቅርቦት በዶሮ እርባታ ተሰማርቶ ውጤታማ መሆኑን የሚናገረው የመርሃ-ግብሩ ተጠቃሚ ሸጋው ካሴ ነው።
አሁን ላይ ከ1ሺ በላይ የ45 ቀን ጫጩቶችን በማሳደግ ለተለያዩ አካባቢዎች በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ መሆኑን ጠቁሞ፣በቀጣይ ሥራውን አስፍቶ ለመስራት ማቀዱን ገልጿል።
የደቡብ ወሎ ዞን እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ ተወካይ ስዩም በቀለ፣ በሌማት ትሩፋት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትንና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዞኑ ከ148 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የመስሪያና የመሸጫ ቦታ እንዲሁም የብድር አቅርቦት በማመቻቸት በዘርፉ እንዲሰማሩና ዘላቂ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ መደረጉንም ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በሌማት ትሩፋት ወተት፣ ስጋ፣ ማርና የዓሣ ምርት ለገበያ መቅረቡን አብራርተዋል።