ምክር ቤቱ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ እንዲሆን ሚናውን ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ እንዲሆን ሚናውን ያጠናክራል
አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2018(ኢዜአ)፦ የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ እንዲሆን ሚናውን እንደሚያጠናክር የጋራ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ታሪኩ ድምበሩ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባን በምርጫ የጊዜ ሠሌዳው መሠረት ከጥር 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል።
ቦርዱ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት ወሳኝ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው ገልጿል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ታሪኩ ድምበሩ፣ ምርጫ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሰፋ፤ ሀገርንም የሚያጸና ስርዓት ነው ብለዋል።
የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ እና አሳታፊ እንዲሆን ምክር ቤቱ ከአባል ፓርቲዎች ጋር ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መደረሱንና የምርጫ ጉዳይን የሚከታተል ኮሚቴ ማዋቀሩን ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫው አስፈላጊነትን በማመን በምርጫ ሂደቱ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫውን ስኬታማ ለማድረግ አመራሮቻቸው፣ እጩዎቻቸውና አባሎቻቸው በሂደቱ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማነቃቃት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።