ባለፉት የለውጥ ዓመታት የብልጽግና ዕሳቤ መሬት ነክቶ ፍሬ እያፈራ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የብልጽግና ዕሳቤ መሬት ነክቶ ፍሬ እያፈራ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2018(ኢዜአ)፦ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የብልጽግና ዕሳቤ መሬት ነክቶ ፍሬ እያፈራ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ባስተላለፉት መልዕክት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆኑ አስፈጻሚ አካላትን የ2018 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ዛሬ ገምግመናል ብለዋል፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የብልጽግና ዕሳቤ መሬት ነክቶ ፍሬ እያፈራ እንደሆነም ነው የገለጹት።
ለዚህ ደግሞ ተቋማትና የተቋማት መሪዎች ግንባር ቀደም ተዋንያን ናቸው ብለዋል፡፡
የብልፅግና ጉዞ “እየሠራሁ ነው፤ ልሠራ ነበር፤ በመሥራት ላይ ነኝ”፤ የሚሉ ሪፖርቶችን አይቀበልም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተሠራ መታየት፤ ከተከናወነ መዳሰስ አለበት ነው ያሉት፡፡
በ2018 ዓ.ም የአዲስ ዓመት ዋዜማ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አጠናቅቀን በጉባ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን አብስረናል ብለዋል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት እንዲሁም የነዳጅ እና የማዳበሪያ ፋብሪካን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጀምረናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
መንግሥታችን ጀምሮ በፍጥነት መጨረስ መለያው ነው፤ በዚህ እሳቤ የተጠናቀቁትን ሸበሌ ሪዞርትንና አይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫን አስመርቀናል ብለዋል፡፡
በቅርቡም የምናስመርቃቸው አሉ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንገዶች፣ ድልድዮች፣ ግድቦች፣ ቤቶች፣ እየተገነቡ ናቸው ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
የጉባ ብሥራቶች ቀስ በቀስ ሥር ሰድደው ተግባራዊ እየሆኑ ናቸው ሲሉም ጠቁመዋል በመልዕክታቸው፡፡
በዛሬው ግምገማችን የስራ እንቅስቃሴዎቻችንንና ስኬቶቻችንን በልኩ መዝነናል፤ ድክመቶቻችንን ያለ ምሕረት ለማረም ተግባብተናል፤ የመፍትሔ መንገዶችን የሚያመላክትና አዳዲስ ስልቶችን መንደፍ የሚያስችል ገንቢ ምክክር አድርገናል ነው ያሉት።
ባለፉት ዓመታት እና በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ባስመዘገብነው ድል ሳንኩራራ ነገር ግን በልኩ እየተበረታታን በቀጣይ ስድስት ወራት ለላቀ ውጤትና ድል ለመትጋት ተግባብተናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡