በመኸር የለማው በርበሬ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለገበያ መረጋጋት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል - ኢዜአ አማርኛ
በመኸር የለማው በርበሬ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለገበያ መረጋጋት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል
ጎንደር፤ ጥር 25/2018 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በመኸር የለማው የበርበሬ ምርት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለገበያ መረጋጋት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።
በዞኑ በ2017/18 የምርት ዘመን በ22 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ በርበሬ ማልማት መቻሉን በመምሪያው የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ ውኃ አጠቃቀም ቡድን መሪ ሐውልቱ ታደሠ ለኢዜአ ገልጸዋል።
የበርበሬ ምርታማነትን ለማሳደግ አዳዲስ ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መደረጉንም ጠቁመዋል።
በዞኑ በመኸር እርሻ ከለማው የበርበሬ ሰብልም ከ400 ሺህ ኩንታል የሚልቅ ምርት ለገበያ መቅረቡን አስታውቀዋል።
በዚህም መሠረት በምሥራቅና ምዕራብ ደንቢያ እንዲሁም አለፋና ጣቁሳ ወረዳዎች ለገበያ የቀረበው የበርበሬ ምርት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ ለገበያ መረጋጋት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ነው ያረጋገጡት።
ከበርበሬ ምርት ሽያጭ ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት የአለፋ ወረዳ አርሶ አደር ሲሳይ ብዙአየሁ፤ ይህን ሥራም በቀጣይ በማስፋት በይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚተጉ ተናግረዋል።
በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ የጯሂት ቀበሌ አርሶ አደር ሙላት ጌትነት በበኩላቸው፤ የበርበሬ ምርት በገበያ ተፈላጊና አዋጭ በመሆኑ ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጉን አረጋግጠዋል።