ቀጥታ፡

ፋይዳ መታወቂያ የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ወሳኝ ነው

ሰመራ፣ጥር 25/2018(ኢዜአ)፡- ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ  የሴቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው የአፋርና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴት አመራሮች ተናገሩ።

በክልሎቹ ሴቶች የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ እንዲኖራቸው ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አመራሮቹ ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ ነስሮ ኡዳ እንዳሉት ጊዜው የዲጂታል ዘመን በመሆኑ እየተካሄደ የሚገኘው የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ ሴቶችን ባካተተ መልክ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በተለይም በክልሉ ገጠራማ አካባቢዎች የሚገኙ የአርብቶ አደር ሴቶችን በዚህ ረገድ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ክልሉ ደረጃም አንድ ሚሊዮን ሴቶችን የመታወቂያው ባለቤት ለማድረግ በቅንጅት አየተሰራ መሆኑን የገለፁት ኃላፊዋ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ  የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።

ሴቶች ይህንን አገልግሎት በቶሎ በማውጣት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተጀመረው የንቅናቄ ስራም ይጠናከራል ብለዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳ ከተማ አስተዳደር የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ወይዘሮ ፋጡማ መሐመድ በበኩላቸው ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት የተቀላጠፈና የተሳለጠ እንዲሆን አስተዋጽኦ ትልቅ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያሳድጋል ብለዋል።

በአሶሳ ከተማ አስተዳደር የወረዳ አንድ ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ አሙና አብዱልዋሂድ እንዳሉት ፋይዳ መታወቂያ ለሴቶች ያለውን ጠቀሜታ በማስገንዘብ የንቅናቄ ስራዎች እየሰራን ነው ብለዋል።

እሰካሁን ባለው የንቅናቄ ስራ ብዙዎችን የመታወቂያው ባለቤት ማድረግ መቻሉን ገልፀው በቀጣይ ወራት ውሰጥ ግቡን ለማሳካት የተጠናከረ ስራ ይሰራል ብለዋል።

የተለያዩ የሴቶች አደረጃጀቶችን በመጠቀም ሴቶች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት እንዲሆኑ የተጀመረው የንቅናቄ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም