የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር ለእንስሳት ዕርባታና ዝርያ ማሻሻል ተግባራት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር ለእንስሳት ዕርባታና ዝርያ ማሻሻል ተግባራት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2018 (ኢዜአ)፡- የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር ለእንስሳት ዕርባታ እና ዝርያ ማሻሻል ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ በስፋት እየተሠራበት መሆኑን የሰሜን ሸዋ ዞን እንስሳትና ዓሣ ሀብት መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የእንስሳት ዕርባታ ቡድን መሪ ቤተልሔም አሰፋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ መርሐ-ግብሩ ለእንስሳት ዕርባታ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ አርሶአደሩ ዝርያን የማሻሻል ተግባራት ላይ በትኩረት እየሠራ ነው።
የሌማት ትሩፋቱን ተከትሎ የተፈጠረው ምቹ የእንስሳት ዕርባታና ዝርያ ማሻሻል ሥራ፤ የእንስሳትን ቁጥርና ጥራት በመጨመር፣ የወትት እና የሥጋን ምርታማነት በማሳደግ የአርሶአደሩ ገቢ እንዲሻሻል አስችሏል ነው ያሉት።
እንደዞን የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል እንዲሁም ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መምጣቱንም ነው ያረጋገጡት።
በዞኑ የባሶና ወራና ወረዳ አርሶ አደር ታደሠ ማሞ እንዳሉት፤ በተሻሻለ ዝርያ ሁለት ላሞችን በማዳቀል በቀን ከአንድ ላም 17 ሊትር ወተት እያገኙ ነው።
የወተት ምርቱን ለገበያ በማቅረብም ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
የሌማት ቱሩፋት መርሐ-ግብሩ ከእንስሳት ቁጥር ይልቅ ጥራት ላይ በማተኮር ምርታማነትን ለማሳደግ እንዳስቻላቸውም ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ተዳቅለው ከሚታለቡ ሁለት ላሞች ከቤት ፍጆታ ባለፈ በቀን በርካታ ሊትር ወተት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ጌታቸው ማሞ ናቸው ።