የበጋ መስኖ ስንዴን በስፋት በኩታ ገጠም በማልማት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየሠሩ መሆናቸውን አርሶአደሮች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የበጋ መስኖ ስንዴን በስፋት በኩታ ገጠም በማልማት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየሠሩ መሆናቸውን አርሶአደሮች ተናገሩ
ጭሮ፤ ጥር 25/2018 (ኢዜአ)፡- ካለፈው ዓመት ልምድ በመውሰድ የበጋ መስኖ ስንዴን በስፋት በኩታ ገጠም በማልማት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሠሩ መሆናቸውን በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የጡሎ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ።
አርሶአደሮቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ያለፈው ዓመት የኩታ ገጠም እርሻ ምርታማነታቸውን በመጨመሩ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት የተሻለ ምርት ለማግኘት መነሳሳት ፈጥሮልናል ብለዋል።
በወረዳው የኢፋ አንዶዴ ቀበሌ አርሶ አደር ጌታቸው አበበ እንዳሉት፤ የግብርና ባለሙያዎች ግንዛቤና ድጋፍ በትንሽ ማሳቸው ላይ ብዙ ማምረት አስችሏቸዋል።
የመስኖ ልማቱን ለማሳካት የውኃ መሳቢያ ሞተር ከወረዳው ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።
ሌላኛው አርሶ አደር ሲራጅ አሊ በበኩላቸው፤ ባለፈው ዓመት ያመረቱት ምርት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸው ዘንድሮ ይበልጥ መነቃቃት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን ሰብሉን ከአረምና ከበሽታ በመጠበቅ የበለጠ ምርት ለማግኘት እየሠሩ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
አርሶ አደሩ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በመሰማራት ገቢውን እንዲያሳድግ የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን የጡሎ ወረዳ ግብርና እና መሬት ጽሕፈት ቤት የእርሻ ከፍተኛ ባለሙያ የኔሁሉ ዘሪሁን አስታውቀዋል።
አርሶ አደሮቹ በትንሽ መሬት ብዙ ምርት በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሙያ እገዛ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በወረዳው በዘንድሮው ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ከታቀደው 700 ሔክታር ማሳ ውስጥ አብዛኛው በዘር መሸፈኑን የተናገሩት ደግሞ የጡሎ ወረዳ ምክትል አሥተዳዳሪ ሸምሰዲን ኡስማን ናቸው።
አርሶ አደሮቹ ከልማቱ በይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምርጥ ዘር እና ፀረ-አረም መድኃኒት እንደቀረበላቸው ተናግረዋል።
እንደዞን ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከተዘጋጀው 38 ሺህ ሔክታር በላይ ማሳ እስካሁን 37 ሺህ ሔክታሩ በዘር ተሸፍኖ እየለማ መሆኑን የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት የስንዴ ልማት አስተባባሪ ሀቢብ አብዱል ከሪም ገልፀዋል።