ቀጥታ፡

የሐረማያ ሐይቅ የቱሪስት መዳረሻነት የማበልጸግ ስራ በተቀናጀ መንገድ በመከናወን ላይ ይገኛል

ሐረማያ ፤ጥር 25/2018 (ኢዜአ) ፡-የሐረማያ ሐይቅን የቱሪስት መዳረሻነቱን የማበልጸግ ስራ በተቀናጀ መልኩ እየተካሔደ መሆኑን  የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።

በማያ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙት የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል የሐረማያ ሃይቅ እንዱ ነው።

ለበርካታ ዓመታት ደርቆ የነበረው ሐይቁ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች ትኩረት ተደርጎ በመከናወናቸው ወደ ቀድሞው ይዞታው መመለስ ችሏል።

የከተማ አስተዳደሩ እና የአካባቢው ማህበረሰብ ሃይቁን እያለማውና እየተንከባከበው በመሆኑም የጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን  የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምቢሩ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ሐይቁ ከመዝናኛነቱ ባለፈ ለወጣቶች የስራ እድል እየፈጠረ የሚገኝ ሲሆን በዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የማጎልበት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

አካባቢው ትልልቅ እሴቶችና ጸጋዎች የሚገኙበትና በኪነ ጥበቡም ዘርፍ ስመ-ጥር አርቲስቶች የፈለቁበት  መሆኑንም ይገልፃሉ።

የአካባቢውን ባህል፣ ኪነ ጥበቡብና ቱሪዝሙ ዘርፉን እንደ አንድ ጸጋ በመጠቀምና ከቱሪዝም ጋር በማሰናሰል የዘርፉን ኢኮኖሚ ማሳደግና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

የማያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢፍራህ ወዚር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአፈርና ውሃ ጥበቃ እና በአረጓዴ አሻራ ስራ የተመለሰውን የሐረማያ ሃይቅ አጠቃቀምን የማስተካከል፣ የመጠበቅና የመንከባከብ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

ሐይቁ ወደ ቀድሞ ቦታው መመለሱ ለጎብኚዎች እርካታን ከማጎናጸፉ ባለፈ ለአካባቢው ነዋሪዎችና ለወጣቶች የገቢ ምንጭ እየሆነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የሐረማያ ሐይቅ በተደረገለት እንክብካቤ ውብና ማራኪ የቱሪስት ቀልብ የሚስብ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ ለወጣቶችም የገቢ ምንጭ ማግኛ ሆኗል ያለው ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ባለሙያ ኦሊያድ በሪሶ ናቸው።


 

በአካባቢው ባለሀብቶችን በመጋበዝ ሎጆችና ሪዞርቶች በማስፋፋት የተሻሉ ስራዎችን መስራት እንደሚቻልም ነው አቶ ኦሊያድ አስተያየታቸውን የሰጡት።


 

በሐረማያ ሐይቅ ላይ የጀልባ አገልግሎት የሚሰጠው ወጣት ሙርቲ አህመድ፤ጎብኚዎችን በጀልባ ከማስጎብኘት ስራ በተጨማሪ በአሳ ልማት ስራም መሰማራቱን ይገልፃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም