ቀጥታ፡

የኢንዱስትሪ ፓርኩን የኃይል አቅርቦት አስተማማኝ ለማድረግ የሚያስችል ዝርጋታ ተከናወነ

አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2018 (ኢዜአ)፡- የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክን የኃይል አቅርቦት አስተማማኝ ለማድረግ የሚያስችል የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ዝርጋታ መከናወኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አንዋር አብራር፥ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከዚህ በፊት ከአዋሽ መልካሳ ማከፋፋያ ጣቢያ ኃይል ሲያገኘ መቆየቱን አውስተው፤ የራሱ ብቸኛ መስመር ባለመኖሩ የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ያጋጥመው ነበር ብለዋል፡፡


 

አሁን ላይ ከአዳማ ቁጥር 3 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በቀጥታ አራት ባለ 33 ኪሎ ቮልት መካከለኛ መስመሮች ለፓርኩ በመዘርጋት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲኖረው መደረጉን ለኢዜአ ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ዝርጋታው 56 ነጥብ 25 ኪሎ ሜትር መሸፈኑን ጠቁመው፤ በዚህም 800 ባለ 12 ሜትር እና 500 ባለ 14 ሜትር አጠቃላይ 774 የኮንክሪት ምሰሶዎች ተከላ መከናወኑን ገልጸዋል።


 

ማከፋፈያ ጣቢያው 40 ሜጋ ዋት ኃይል ለፓርኩ በቀጥታ ማቅረብ የሚያስችል ዐቅም እንዳለውም አስረድተዋል።

ይህም አምራች ኢንዱስትሪዎቹ አሁን የሚጠቀሙትን የኃይል መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግና ተጨማሪ አምራቾች ለመሳብ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡


 

የተዘረጋው የኤሌክትሪክ መስመር የፓርኩን የኃይል አቅርቦት አስተማማኝ ከማድረግ ባሻገር በፓርኩ ተሰማርተው ለሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተጨማሪ ዐቅምን ለመፍጠር፣ ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለማስፋፋትና ኢኮኖሚውን ለመደግፍ እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።

የሀገራችን ኢኮኖሚ እያደገ እና ኢንዱስትሪዎች እየሰፉ መሄዳቸውን ተከትሎ ዘላቂ እና ከፍተኛ ጥራት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ፤ ተቋማችን እነዚህን ፍላጎቶች በፍጥነት፣ በፈጠራ እና በቅልጥፍና ለማሟላት በቁርጠኝነት እየሠራ ነው ሲሉም አስታውቀዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም