የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን ውጤታማነት ለማስቀጠል የድጋፍና ክትትል ስራው ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን ውጤታማነት ለማስቀጠል የድጋፍና ክትትል ስራው ይጠናከራል
ወልቂጤ ፤ጥር 25/2018 (ኢዜአ)፡- የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ውጤታማነት ለማስቀጠል የድጋፍና ክትትል ስራው እንደሚጠናከር የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
የክልሉ ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር አምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን አምስተኛ መደበኛ ጉባዔውን በወልቂጤ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
የምክር ቤቱ ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎ፤ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፤ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ውጤታማነት ለማስቀጠል የድጋፍና ክትትል ስራው ይጠናከራል።
የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች መደበኛና ድንገተኛ የመስክ ምልከታዎችን በማድረግ ምርጥ ተሞክሮዎችን በማስፋትና ክፍተቶች ሲገኙም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይ አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት የህዝብና የመንግስት ሃብት በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉን ለማረጋገጥም የክትትልና ቁጥጥር ስራ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የበጋ መስኖን ጨምሮ በሰብል ልማት፣ በእንስሳትና በሌማት ትሩፋት የተከናወኑ ተግባራት ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ መሆናቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡
የተጀመሩ የውኃ፣ የመንገድና ድልድይ እንዲሁም የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ክትትልና ቁጥጥር በመደረጉ የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች የህዝብ ተሳትፎ የተረጋገጠባቸው፣ ለወጣቶች የስራ እድል የፈጠሩና የከተሞችን ገጽታ የቀየሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አሰራርን በማዘመን በአገልግሎት ዘርፍ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ እየተከናወነ ያለው ተግባርም ተስፋ ሰጪ ውጤት የታየበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አፈ-ጉባኤዋ አክለውም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና አርዓያነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የምክር ቤት አባላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡
ለሁለት ቀናት የሚካሔደው ጉባኤም የ2018 በጀት ዓመት ስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ላይ የሚመክር ሲሆን የተለያዩ አዋጆችና ሹመት መርምሮ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።