ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች ምርታማነት እንዲጎለብት አግዘዋል

‎ባህር ዳር፤ጥር 25/2018 (ኢዜአ)፡- አማራ ክልል የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርታማነት እንዲጎለብት እገዛ ማድረጋቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

‎የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት፤ ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች  የአፈር ለምነትን  በመጨመር ምርታማነት እንዲያድግ አግዘዋል።

‎ስራውን በማስቀጠልም ‎በያዝነው የበጋ ወራት በተለዩ ዘጠኝ ሺህ 206 ተፋሰሶች በ456 ሺህ 411 ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ለማከናወን ግብ ተይዞ  ወደ ተግባር ተገብቷል።


 

‎እስካሁን በተደረገ ጥረትም የዕቅዱን 37 በመቶ ማከናወን እንደተቻለ ጠቅሰው፤ በዚህም ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ገልፀዋል። 

‎ከዚሁ በተጓዳኝም ለመጪው ክረምት ወራት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ የሚሆን ቦታ የመለየትና ለተከላ የሚውል ከ አንድ ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን አንስተዋል።

በተቀናጀ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ላይ ከተሰማሩ  አርሶ አደሮች መካከል ‎በደቡብ ጎንደር ዞን የፋርጣ ወረዳ አርሶ አደር ዓለሙ መንጌ በበኩላቸው፤ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ከህልውና ጋር የተያያዘ መሆኑን በመረዳት ተግባሩን በማጠናከር በየዓመቱ በራሳቸው ተነሳሽነት እያከናወኑ መሆናችውን አንስተዋል። 

‎ዘንድሮም በቀበሌያቸው በተጀመረው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ላይ በንቃት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።  

ባለፉት ዓመታት በቀበሌያቸው ያከናወኑት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ የመሬቱን ለምነት በመመለስ ለምርታማነት ማደግ አስተዋጽኦ እንዳበረከተላቸው የገለፁት ደግሞ ‎ሌላኛው የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ካሳሁን መንግስት ናቸው። 

ቀደም ሲል የተሰራው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ግማሽ ሄክታር የእርሻ ማሳቸውን ለምነት በመመለሱ እስከ አምስት ኩንታል ተጨማሪ ምርት እንዲያገኙ ማስቻሉን ገልፀዋል።

የልማት ስራው ተጠቃሚነታቸውን በተጨባጭ እያሳደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።

‎በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተከናወነ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራም የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባሻገር በግብርና ምርታማነት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ እንዳስቻለም ተመላክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም