ሀገራዊ ምርጫው ፍትሐዊና ገለልተኛ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት ወሳኝ ሚና መጫወት ይገባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምርጫው ፍትሐዊና ገለልተኛ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት ወሳኝ ሚና መጫወት ይገባቸዋል
አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2018 (ኢዜአ)፦ 7ኛው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት ወሳኝ ሚና መጫወት እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የጸጥታ ሁኔታን ለመገምገም ያለመ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የጸጥታ አካላት የሥራ ኃላፊዎችና የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች ታድመዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በስኬት ማካሄድ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
ለዚህም በ7ኛው ሀገራዊ የምርጫ ዝግጅት መነሻነትም የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ይፋ በማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም የመራጮችን የምርጫ ግንዛቤ የሚያሳድግ ትምህርትና ስልጠና መስጠት የሚችሉበትን ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
ለፖለቲካ ፓርቲዎችም የምርጫ ተሳትፎን የሚያጠናክር ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክም በየአካባቢው ያለውን ነባራዊ ሁኔታን የሚዳስስ ግንዛቤ የሚፈጠርበት መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም 7ኛው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት ወሳኝ ሚና መጫወት እንደሚገባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።