ቀጥታ፡

ህዝቡ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና የዳበረ ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲኖረው እየሰራን እንገኛለን -ሲቪክ ማህበራት

አርባምንጭ ፤ጥር 25/2018 (ኢዜአ):- ህዝቡ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዳበረ፣ ስልጡን እና ሰላማዊ ተሳትፎ እንዲኖረው ለማድረግ እየሰራን ነው ሲሉ   በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ የሲቪክ ማህበራት ገለጹ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች እንዳሉት፤ ህዝቡ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዳበረ፣ ስልጡን እና ሰላማዊ ተሳትፎ እንዲኖረው የተጠናከሩ ስራዎችን በመስራት የድርሻችንን እየተወጣን እንገኛለን ብለዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ናና 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ነፃ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን እየተወጣን ነው ብለዋል።

በተለይም በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫው ወቅትና እና በድህረ ምርጫው ጊዜ ዜጎች በሰለጠነ መንገድ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለዚህም መንግስት የሲቪል ማህበረሰቡን ሚና ለማጎልበት ከዚህ ቀደም ከነበረው የላቀ እውቅና መስጠቱ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ልዕልና በር ከፋች ነው ብለዋል።

በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከህዝብ የተወለዱ ሀገር በቀል ድርጅቶች እንደመሆናቸው የምርጫው ሂደት ሰላማዊና ፍትሃዊ እንዲሆን በልዩ ትኩረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶች ተሳትፎ ጎልቶ እንዲወጣ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር ወይዘሮ መነን ዘውዱ ናቸው።

ሴቶች የመምረጥና የመመረጥ መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ብሎም ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና አካታች እንዲሆን ከአንድ ሚሊዮን ለሚልቁ የማህበሩ ሴት አባላት የግንዛቤ መፍጠር ስራ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።

ድምጾቹ የሀገርን ህልውና የሚወስኑ መሆናቸውን የጠቀሱት ሊቀመንበሯ በሀገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ልምምድን ለማጽናት በሚደረገው ጥረት የሴቶች ድርሻ ጎልቶ መውጣት እንዳለበትም አመልክተዋል።

የክልሉ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፀሐፊ ወጣት አማኑኤል ሳሙኤል፤ ሀገራዊ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ አካታች፣ ነፃና ገለልተኛ እንዲሆን ወጣቱን ባማከለ መልኩ ትኩረት መደረጉን ገልጿል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የወጣቱ ሚና ወሳኝ በመሆኑ በሀገራዊ ምርጫው የበኩሉን እንዲወጣ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ነው የገለፀው ።

በዚሁ ወቅት ዜጎች ይወክለናል የሚሉትን እንዲመርጡ በምርጫው አስፈላጊነትና ህጎች ዙሪያ ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑንም አመልክቷል።

  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም