ዓመታዊ ግብርን በየሩብ ዓመቱ መክፈላቸው ጫና እንደቀነሰላቸው ግብር ከፋዮች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ዓመታዊ ግብርን በየሩብ ዓመቱ መክፈላቸው ጫና እንደቀነሰላቸው ግብር ከፋዮች ገለጹ
ወልዲያ፤ ጥር 25/2018 (ኢዜአ)፡- ዓመታዊ ግብርን በየሩብ ዓመቱ መክፈል የሚያስችል አሠራር መተግበሩ ግብራቸውን ያለጫና መክፈል እንዳስቻላቸው የሰሜን ወሎ ዞን ግብር ከፋዮች ተናገሩ።
በሐራ ከተማ በምግብ ቤት ሥራ የተሰማሩት ሰዒድ መሐመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ነጋዴው ባገኘው ትርፍ ልክ ለሀገሩ የሚከፍለው ግብር የሀገሩ ልማት ዋስትና ነው።
ዓመታዊ ግብርን በዓመት አንድ ጊዜ መክፈል ጫና እንደነበረው አውስተው፤ አሁን ላይ በየሩብ ዓመቱ መክፈል የሚቻልበት አሠራር መዘርጋቱ እፎይታ እንደሰጣቸው አስረድተዋል።
በሸቀጣሸቀጥ ንግድ የተሰማሩት ማርታ ሁሴን በበኩላቸው፤ ዓመታዊ ግብር በየሩብ ዓመቱ የሚከፈልበት ሁኔታ መዘርጋቱ ለነጋዴው ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንና ግብሩን በወቅቱ ለመክፈል ማስቻሉን ገልጸዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ገቢዎች መምሪያ የግብር ትምህርትና ኮሙኒኬሽን ቡድን መሪ ፍቅር መንግሥቴ፤ ግብር ከፋዩ የተጣለበትን ግዴታ በኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የነበረው የግብር አሰባሰብ በየሩብ ዓመቱ እንዲሆን የተዘረጋው አሠራር ነጋዴው ሳይጨናነቅ ግብሩን እንዲከፍል ማድረጉንም አስረድተዋል።
በዞኑ በተያዘነው በጀት ዓመት 3 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱንም አመላክተዋል።