ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ፣ የተፋሰስ ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የውሃ አዘል መሬቶችን ከመጠበቅ አኳያ ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2018 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ፣ የተፋሰስ ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የውሃ አዘል መሬቶችን ከመጠበቅ አኳያ ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ መሆኑን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ፡፡ 

ባለስልጣኑ የዘንድሮውን የዓለም የውሃ አዘል መሬቶች ቀን "የውሃ አዘል መሬት እና ሀገር በቀል እውቀት፤ የባህል ቅርሳችንን እናክብር" በሚል መሪ ቃል እያከበረ ይገኛል። 

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬነሽ መኩሪያ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ የውሃ አዘል መሬቶች እና የብዝሃ ህይወት ባለቤት ናት። 


 

እነዚህ ተፈጥሯዊ ጸጋዎች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሸጋገሩም ሀገር በቀል እውቀት እና ባህላዊ የጥበቃ ስልቶች ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

የውሃ አዘል መሬቶች ከፍተኛ ጥቅም እያስገኙ መሆኑን ጠቁመው የተበከለ ውሃን በተፈጥሯዊ መንገድ ማጣራት፣ የጎርፍ አደጋን መከላከል እና የአፈር እርጥበትን መጠበቅ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እና የአካባቢን ሙቀት መቀነስን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ 

በእነዚህ ወሳኝ የተፈጥሮ ሃብቶች ላይ የሚደርሱ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ዘመናዊውን ሳይንሳዊ እውቀት ከሀገር በቀል ጥበብ ጋር አቀናጅቶ መተግበር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበሩ ያሉ የአረንጓዴ አሻራ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች ለውሃ አዘል መሬቶች ደህንነት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን አረጋግጠዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቴ ግጄ፤ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ውሃ አዘል መሬቶችን የመለየትና ተገቢውን ጥበቃ የማድረግ ተግባር በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።



 

የአማራ ክልል የአካባቢ ጥበቃና ደን ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ በልስቲ ፈጠነ በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚገኙ የውሃ አዘል ስፍራዎችን በዘላቂነት ለማልማት ዘመናዊ ሳይንሳዊ ዕውቀቶችን ከባህላዊ ጥበቃ ዘዴዎች ጋር በማቀናጀት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

ማህበረሰቡ ስለ እርጥብ መሬቶች ፋይዳ ያለውን ግንዛቤ እንዲያሳድግና ከሀብቱ በሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆን ሰፊ የትምህርትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኦሮሚያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ኢዳቲ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም