ነገሌ አርሲ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሶስተኛ ከፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ነገሌ አርሲ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሶስተኛ ከፍ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ነገሌ አርሲ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2 ለ 0 አሸንፏል።
ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ከቤ ብዙነህ በጨዋታ እና ዳዊት ተፈራ በፍጹም ቅጣት ምት የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
በሊጉ ተከታታይ ድሉን ያስመዘገበው ነገሌ አርሲ በ32 ነጥብ ደረጃውን ከአራተኛ ወደ ሶስተኛ ከፍ አድርጓል። በውድድር ዓመቱ ዘጠነኛ ድሉን አስመዝግቧል።
በአንጻሩ በሊጉ ስድስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ20 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ተጠባቂ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስን 1 ለ 0 አሸንፏል።
የቅዱስ ጊዮርጊሱ ቶሎሳ ንጉሴ በ82ኛው ደቂቃ በራሱ ላይ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።
በውድድር ዓመቱ ስምንተኛ ድሉን ያስመዘገበው ፋሲል ከነማ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ32 ነጥብ ከነበረበት አምስተኛ ደረጃ ወደ አራተኛ ከፍ ብሏል።
በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ለሰባተኛ ጊዜ የተሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ23 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች አላሸነፈም።
በሌላኛው መርሐ-ግብር መቀሌ 70 እንደርታ እና ኢትዮጵያ ቡና አንድ አቻ ተለያይተዋል።
የኢትዮጵያ ቡናው በፍቃዱ አለማየሁ በራሱ ላይ ለመቀሌ 70 እንደርታ፣ አምበሉ ራምኬል ጀምስ ለኢትዮጵያ ቡና ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
መቀሌ 70 እንደርታ በ18 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ኢትዮጵያ ቡና በ20 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል።
ቀን ላይ በተደረገ የመጀመሪያ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን 2 ለ 1 በመርታት በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል።
ጨዋታዎቹን ተከትሎ 18ኛ ሳምንት ተጠናቋል።
የ19ኛ ሳምንት እና የሊጉ የመጀመሪያ ዙር የማጠናቀቂያ መርሐ-ግብር ከጥር 27 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ይካሄዳል።