ቀጥታ፡

ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የጤና  አገልግሎትን ተደራሽነት ለማሳካት ለጤና መድህን አገልግሎት ትኩረት ተሰጥቷል

ሰመራ፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፦በአፋር ክልል ለአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የጤና አገልግሎትን ተደራሽነትና ጥራት ለማሳካት ለጤና መድህን አገልግሎት ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ።

በኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የአፋር ክልል ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀምና የቀጣይ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን እንደተናገሩት፤ በክልሉ የህብረተሰብ  ጤና  አገልግሎትን ተደራሽነትና ጥራት ለማሳካት  ለጤና መድህን አገልግሎት ትኩረት ተሰጥቷል።

ለዚህም በክልሉ ባሉ ሁሉም ወረዳዎች አገልግሎቱን ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊው እገዛ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አቶ ዊቲካ ኖሬ በበኩላቸው፤ የክልሉን ማህበረሰብ የጤና  አገልግሎት ጥራትና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በቅንጅት መሰራቱን አንስተዋል።


 

ተግባሩን በማጠናከር የጤና አገልግሎቱን ውጤታማ ለማድረግ  አሰራሩን የማዘመንና የጤና መድህን አገልግሎትን ለማስፋፋት  መሰራቱን ተናግረዋል።

በዚህም በክልል ደረጃ  የተጠቃሚ  አባዎራዎችና እማዎራዎችን ቁጥር ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የአመራሩን ቁርጠኝነት  እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ያምሮት አንዷለም  እንዳሉት፤ እንደ ሀገር የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎትን ፍትሃዊነትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ  እየተሰራ  ነው።


 

በአፋር ክልልም አገልግሎቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ መረጃዎች በአንድ ቋት ውስጥ የማካተት ስራ መከናወኑን  ጠቁመዋል።

በክልሉ  የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ያልሆኑ ወረዳዎችን  ወደ ስራው ለማካተት  በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በመድረኩ የአፋር ክልል ከፍተኛ የስራ ኀላፊዎችና የወረዳ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም