ቀጥታ፡

የግብርና ምርታማነትንና የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተቀየሱ ስትራቴጂዎች እየተተገበሩ ነው

አዳማ፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፡- የግብርናን ምርታማነትና የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተቀየሱ ስትራቴጂዎች እየተገበሩ መሆኑን የተለያዩ ክልሎች የግብርና ቢሮ አመራሮች አስታወቁ።

የግብርና ሜካናይዜሽን እና የከተማ ግብርና ስትራቴጂዎች፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የገቢ ምርቶችን ለመተካት እና የወጪ ንግድን ለማሳደግ የጎላ ሚና እንዳላቸው ይታመናል።

በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር እንዳሉት፤ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ኢኮኖሚያዊ  ጠቀሜታውን ለማሳደግ የግብርና ሜካናይዜሽን እና የከተማ ግብርና ጉልህ ድርሻ አላቸው።

ቀደም ሲል ሲሠራ የነበረውን የግብርና ሜካናይዜሽን እና የከተማ ግብርናን በተደራጀ አግባብ ለማስፈጸም የተዘጋጁ ስትራቴጂዎች ተጨማሪ ዐቅም እንደሆኑም አንስተዋል።

የከተማ ግብርና ስትራቴጂው ከተሞች ሸማች ብቻ ሳይሆኑ አምራች እንዲሆኑና የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ  የሚደረገውን ግብ ለማሳካት አበርክቶው የጎላ መሆኑንም ለኢዜአ ተናግረዋል።

የከተማ ግብርና ከኢኮኖሚው ባሻገር የሥነ-ምኅዳር ሚዛንን ለመጠበቅ፣ የሥራ ባህል ለማሻሻል እና የሀብት ምንጭ በመሆንም በርካታ ፋይዳ እያስገኘ መሆኑን አስረድተዋል።   


 

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ በሪሶ ፈይሳ በበኩላቸው፤ የከተማና የገጠር ግብርና ልማትን ለማሳደግ ሁሉንም አካል ያሳተፈ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይም የዘርፉን የአሠራር ሥርዓት አካታችና አሳታፊ በማድረግ የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ የሚወጡ ስትራቴጂዎችን በዕቅድ በማስደገፍ ለተግባራዊነቱ በክልሉ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በክልሉ ሜካናይዜሽንን ለማስፋት በየደረጃው በተደረገው ጥረት አሁን ላይ 50 በመቶ የሚሆነው የእርሻ መሬት በሜካናይዜሽን ታግዞ እየለማ መሆኑንም ለአብነት አንስተዋል።

ይህም ምርታማነትን ለማሳደግና የምርት ብክነትን በማስቀረት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ አስችሏል ብለዋል።

በቀጣይም ለግብርና ሜካናይዜሽን እና ለከተማ ግብርና ስትራቴጂ ተፈጻሚነት አበክረን በመሥራት የዘርፉን ምርታማነት እናረጋግጣለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም