መንግስት ለባህላዊ ፍርድ ቤቶች የሰጠው ህጋዊ እውቅና ለፍትህ ስርዓቱ ተደራሽነት ተጨማሪ አቅም ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለባህላዊ ፍርድ ቤቶች የሰጠው ህጋዊ እውቅና ለፍትህ ስርዓቱ ተደራሽነት ተጨማሪ አቅም ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፦ መንግስት ለባህላዊ ፍርድ ቤቶች የሰጠው ህጋዊ እውቅና ለፍትህ ስርዓቱ ተደራሽነት ተጨማሪ አቅም መፍጠሩን የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ውስጥ ሽምግልና፣ የገዳ ሥርዓት፣ አበጋርና ሌሎችም ባህላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች እንደ ማህበረሰቡ ዋና እሴቶች ሆነው ዘልቀዋል፡፡
ይሁን እንጂ መንግስታት ሲለዋወጡ ዘመናዊ የሕግ ሥርዓትን ለመከተል በሚያደርጉት ጥረት፣ ለባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች የሚሰጣቸው ትኩረትና ተቀባይነት እየቀነሰ ቆይቷል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ዳይሬክተር ኖህ ታከለ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በማህበረሰቡ ዘንድ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ዘላቂ ግንኙነትን በሚያጠናክር መንገድ የሚፈቱባቸው ሥርዓቶች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች ለዘመናት ማህበረሰቡን በሰላምና በአብሮነት አጽንተው የቆዩ ጥንታዊ እሴቶች ቢሆኑም፣ አሁን ላይ መንግሥት ሕጋዊ ዕውቅና መስጠቱ ለፍትሕ ሥርዓቱ ተደራሽነትና ጥራት አዲስ አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በርካታ ዜጎች በባህላዊ የግጭት አፈታት ስልቶች በሚሰጡ ውሳኔዎች ደስተኛ መሆናቸው በጥናት ተለይቷል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህም ማህበረሰቡ ለባህሉና ለእሴቱ የላቀ ቦታ እንደሚሰጥ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወኑ የፍትሕ ዘርፍ ሪፎርሞች እነዚህ እሴቶች ለሰላምና መረጋጋት ያላቸውን አበርክቶ ታሳቢ በማድረግ፣ በቂ ትኩረት ተሰጥቷቸው የትግበራ ሕግ እንዲወጣላቸው ተደርጓል ብለዋል፡፡
የባህላዊ ፍርድ ቤቶች የመንግሥትንና የዜጎችን ወጪ የሚቀንሱ በመሆናቸው፤ በአሁኑ ወቅት ወደ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የሚሄዱ ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር ክልሎች የራሳቸውን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ሕግ እንዲያወጡ ሞዴል ሕግ ማዘጋጀቱን በመጥቀስ፤ ስምንት ክልሎች እስካሁን ተግባራዊ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ክልሎቹ ያወጧቸው ሕጎች ከሕገ-መንግሥቱ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውንና የዜጎችን ፍላጎት ማርካታቸውን በጥናት በመለየት ለባህላዊ የግጭት አፈታት ስልቶች ዕውቅና እንደሚሰጡ አስረድተዋል፡፡
በአንዳንድ ክልሎች ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ከመደበኛው ፍርድ ቤት ጋር ተቀራራቢ የሆኑ የክስ መዝገቦችን እየተመለከቱ መሆኑን በማንሳት፤ ለአብነት በኦሮሚያ ክልል ከ7 ሺህ በላይ ቀበሌዎች የባህላዊ ፍርድ ቤት መዝገብ ማደራጀታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በመጀመሪያና በይግባኝ ደረጃ በተቋቋሙ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የተላለፉ ውሳኔዎች በፈቃደኝነት የማይፈጸሙ ከሆነ፣ መደበኛው ፍርድ ቤት ውሳኔዎቹን የማስፈጸም ግዴታና መብት ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ዘርፍ ኮሚሽነር አብዲ ጅብሪል (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች መቋቋም የፍትሕ ተደራሽነትን በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል፡፡
ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበርና ለማስከበር የፍትሕ ተደራሽነት ቀዳሚ ተግባር መሆኑን በመጥቀስ፤ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ሰብዓዊ መብቶችን ለማስተማርና ግንዛቤ ለመፍጠር ወሳኝ መድረክ እንደሚሆኑም አብራርተዋል፡፡
ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው በመሆናቸው፣ ተገቢው ዕውቅና ተሰጥቷቸው በሕግ ማዕቀፍ እንዲቋቋሙ መደረጉ ተገቢ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡