ቀጥታ፡

ፓርቲው  በክልሉ የፖለቲካና የአደረጃጀት ስራዎችን በብቃት በመምራት  የላቀ ውጤት አስመዝግቧል

ቦንጋ፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፦ፓርቲው የፖለቲካና የአደረጃጀት ስራዎችን በብቃት በመምራት በልማትና በመልካም አስተዳደር ስራዎች የላቀ ውጤት ማስመዝገቡን በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል  ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቅሬ አማን ተናገሩ፡፡

በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡


 

በመደረኩ ላይ  ንግግር ያደረጉት በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍቅሬ አማን እንደገለፁት፣  ፓርቲው በሀገርም ሆነ በክልል ደረጃ  ለውጡን በመምራት  አሻጋሪ ተግባራትን  በቅንጅት እየሰራ  ነው።

ለዚህም   ዘርፈ ብዙ ሪፎርሞችን  በመተግበር   የፖለቲካ ምህዳሩን  ለማስፋትና ተተኪ አመራር ለመፍጠር ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል። 

በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት በፖለቲካ አቅም ግንባታ ዘርፍ፣ በዲሞክራሲ ባህል ግንባታና በሌሎችም ዘርፎች በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን   አንስተዋል።

የሰለጠነ የፖለቲካ ስርአት  ለመገንባት  በሚደረገው ጥረት  ለአባላቱና ደጋፊዎቹ  ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ በማድረግ  የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።


 

የፖለቲካና የአደረጃጀት ስራዎችን በብቃት በመምራት በልማትና በመልካም አስተዳደር ስራዎች የላቀ ውጤት መምጣቱን  ጠቁመዋል።

7ኛው ጠቅላላ  ምርጫ ዲሞክራሲያዊ፣ ተአማኒና ነፃ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፓርቲው  ሚናውን  እንደሚወጣ ተናግረዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት  የስትራቴጂክ ስራ አመራር ዘርፍ ሀላፊ አቶ አንተነህ አየለ፤ የስድስት ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት፣ የአባላቱንና አመራሩን  አቅም በማሳደግና  በማሳተፍ  የተከናወኑ ተግባራት  ውጤታማ  እንደነበሩ አንስተዋል። 


 

የፓርቲውን አመራርና አባላትን የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ለመፍጠር የተደረጉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ያመጡትን ለውጥ ለማስቀጠል እንደሚሰራም አመልክተዋል።

የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን ለማጠናከር  በሚደረገው ጥረትም   በየደረጃው የሚገኙ  አመራሮችና አባላት የህግና የፓርቲ ስነምግባር መመሪያን  ይበልጥ እንዲያክብሩ በጥብቅ ዲሲፕሊን መመራቱን አንስተዋል።

በመድረኩ ላይ  በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማንን ጨምሮ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም