ቴክኖሎጂን በመጠቀም የዜጎችን የፍትሕ አገልግሎት ቀልጣፋ ማድረግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
ቴክኖሎጂን በመጠቀም የዜጎችን የፍትሕ አገልግሎት ቀልጣፋ ማድረግ ተችሏል
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፡- ቴክኖሎጂን በመጠቀምና የጉዳዮች ፍሰት መመሪያን በመተግበር የዜጎችን የፍትሕ አገልግሎት ቀልጣፋ ማድረግ መቻሉን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሌሊሴ ደሳለኝ ገለጹ፡፡
የፍትሕ ሥርዓቱን በማሻሻል ሕብረተሰቡ የሚያገኘውን አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ ሰፊ የሪፎርም ሥራ መከናወኑን አውስተዋል።
በዚህም መሠረት ባህላዊ የግጭት አፈታት ስልቶች አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶች በመሆን የሕግ ድጋፍና ዕውቅና እንዲኖራቸው ተደርጓል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የፍርድ ቤት አስማሚነትን ተግባራዊ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱ እንዲሻሻል መደረጉንም አስታውቀዋል።
በፌደራልና በክልል ፍርድ ቤቶች በርካታ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ጠቅሰው፤ በፍርድ ቤት አስማሚነት ከፍተኛ የክርክር መጠን ያላቸው ጉዳዮች በስምምነት እንዲፈቱ መደረጉን አረጋግጠዋል።
የፍርድ ቤቶች የሪፎርም ሥራዎች የማኅበረሰቡን የተፋጠነ ፍትሕ ፍላጎት እንዲሻሻል ማስቻላቸውንም አመላክተዋል።
በክርክር አመራርና የውሳኔ ጥራት ላይ ቅሬታዎች ሲነሱ እንደነበር አውስተው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ባለጉዳዮች ጥራት ያለው አቤቱታና መረጃ እንዲያቀርቡ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የሰበር ችሎት ውሳኔዎች በሠነድ ተደራጅተው እንዲቀመጡ በማድረግ ለዐቅም ግንባታና ለውሳኔዎች ተመሳሳይነት ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ የጉዳዮች ፍሰት መመሪያ ተግባራዊ መደረጉ ለሥራው ተጨማሪ ዐቅም እየፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል።