ሀገራዊ ምክክሩ ልማቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስረከብ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ልማቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስረከብ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ምክክሩ ሰላምና ልማቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን የሸገር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
አቶ ከበደ ኩምሳ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ምክክሩ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ትልቅ በር የከፈተ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም ችግሮችን በምክክር በመፍታት ሀገርን በጋራ የመገንባት ሂደት እውን እንዲሆን ምክክሩ የጎላ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ ለስኬቱም የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም የቆዩ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ዘላቂ ሠላምና አብሮነትን ይበልጥ ለማጠናከር ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን ጠቁመው፤ ለነገዋ የበለፀገች ኢትዮጵያ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ጫሊ ወርቅነህ በበኩላቸው፤ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ምክክሩ ችግሮችን በመፍታት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ የሚያስችል ነው ያሉት አስተያየት ሰጭዋ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ለዘላቂ ልማትና ለሕዝቦች አብሮነት ጠንካራ መሠረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ አለመግባባቶችን በምክክር በመፍታት በጋራ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለማጎልበት እየሠራ መሆኑ ይታወቃል።
ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ ጠንካራ ሀገረ መንግሥትን ለመገንባት እና የዴሞክራሲ ባህልን ለማዳበር ትልቅ ዕድል የሚሰጥ መሆኑም ይታመናል።