ለሕብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ለሚመጡ እንግዶች አፍሪካዊ ባህልን የሚያንጸባርቁ አልባሳትና ጌጣጌጦች አዘጋጅተናል- ነጋዴዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለሕብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ለሚመጡ እንግዶች አፍሪካዊ ባህልን የሚያንጸባርቁ አልባሳትና ጌጣጌጦች አዘጋጅተናል- ነጋዴዎች
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፡- ለ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ለሚመጡ እንግዶች አፍሪካዊነትን የሚያንጸባርቁ የባህል አልባሳትና ጌጣጌጦች ማዘጋጀታቸውን የሀገር ባህል አልባሳት ጌጣጌጥ ነጋዴዎች ገለጹ።
በባህል አልባሳት ንግድ የተሰማሩት ይላቅ በሺወርቅ፤ በአዲስ አበባ የሚከናወኑ መድረኮች መበራከት የባህል አልባሳትን ለማስተዋወቅና ገቢ ከማግኘት አንጻር ሰፊ ዕድል መፍጠራቸውን አንስተዋል።
ለአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ለሚመጡ እንግዶችም ጥራት ያላቸው የባህል አልባሳት ማዘጋጀታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ምስጢረ ነጋሽ በበኩላቸው አፍሪካዊ አንድነትን የሚገልጹ ቀለማትና ምልክቶች የታተሙባቸው አልባሳት ማዘጋጀታቸውን ገልጸው፤ ይህም እንግዶች የሀገራቸውን ያህል እንዲሰማቸው ለማድረግ ይረዳል ብለዋል።
ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ እንግዶች የባህል ምርቶችን የመጎብኘትና የመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ነጋዴ ማርታ መንግሥቱ ናቸው።
ለሕብረቱ ጉባዔ የሚመጡ እንግዶችን በታማኝነት በማስተናገድ የሀገራችንን ገጽታ ከመገንባት ጎን ለጎን ምርቶቻችንን ለማስተዋወቅ ተዘጋጅተናል ብለዋል።
በባህል ጌጣጌጦችና አልባሳት ንግድ የተሰማሩት ሳራ ብርሃኑ እና ፍሬው ለማ በበኩላቸው፤ የኢትየጵያን ብዝኃ-ባህል የሚወክሉ አልባሳት፣ ቅርፃቅርፆችና ሥዕሎችን አዘጋጅተው እንግዶችን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህ አጋጣሚ የሀገርን ገጽታ ለመገንባት፣ የኢትዮጵያን ባህልና ዕሴት ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።