ቀጥታ፡

ምርታማነትን በማሳደግ የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል

ባሕር ዳር፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፡- በሁሉም ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል አመራሩ ሕዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅበት የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አስገነዘቡ።

የክልሉ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የፓርቲና የመንግሥት ሥራዎች ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

ባለፉት ስድስት ወራት በሁሉም ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ የሕዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በዚሁ ወቅት ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ተናግረዋል።

ለዚህም ክልሉ የ25 ዓመት አሻጋሪና ዘላቂ የልማት ዕቅድና የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በተሻለ ሁኔታ እየተገበረ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለአብነትም በሰብል ልማት፣ በእንስሳት፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና መሰል ሥራዎች ሞዴል የሆኑና ይበልጥ ሊሰፉ የሚችሉ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
 
በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻልና በሌሎች ዘርፎችም የተሻለ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን ነው ያመለከቱት።
 
ችግሮችን በመቋቋም የተገኙ ውጤቶች የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ አሁንም የክልሉን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል።

በመሆኑም የሕዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ የተገኙ ውጤቶችን ማስፋት ይገባል ነው ያሉት።
 
ለዚህም በሁሉም ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ በኩል አመራሩ ሕዝቡን በነቂስ በማነቃነቅ በጋራ መረባረብ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
 
በቀሪ ወራትም በየዘርፎቹ የተቀመጡ ግቦች እንዲሳኩ ትብብርን በማጠናከር መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተለይም በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን በመፍታትና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ርዕሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።


 

በመድረኩ ጥንካሬዎችንና ድክመቶችን በጥልቀት በመመልከት የቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ሊቀመጡ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም