ኢትዮጵያ የቀጣናዊ ብልጽግና ሞተር እና የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ናት- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የቀጣናዊ ብልጽግና ሞተር እና የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ናት- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፡- ከሕልም ወደ እውነት፤ ኢትዮጵያ የቀጣናዊ ብልጽግና ሞተር እና የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ናት ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
አገልግሎቱ ባወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ አዲስና ብሩኅ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች ብሏል።
ትናንት ስናልማቸው የነበሩ ታላላቅ ርዕዮች ዛሬ በተግባር ተተርጉመው የዜጎች ተጠቃሚነት የሚረጋገጥባቸው፣ የሀገር ክብር የሚታደስባቸውና የቀጣናው ትስስር የሚጠናከርባቸው ኅያው እውነታዎች ሆነዋል ሲልም ገልጿል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡-
"ከሕልም ወደ እውነት፡ ኢትዮጵያ የቀጠናዊ ብልፅግና ሞተር እና የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል!”
የኢፌድሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ጥር 24 /2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በታሪኳ አዲስና ብሩህ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። ትላንት ስናልማቸው የነበሩ ታላላቅ ርዕዮች ዛሬ በተግባር ተተርጉመው የዜጎች ተጠቃሚነት የሚረጋገጥባቸው፣ የሀገር ክብር የሚታደስባቸውና የቀጠናው ትስስር የሚጠናከርባቸው ህያው እውነታዎች ሆነዋል።
በትናንትናው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት፣ የቀጠናው ሀገራት መሪዎች በተገኙበት የተመረቁት ግዙፍ ፕሮጀክቶች፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት የመሆን ህልሟን ለማሳካት የያዘችው ጽኑ አቋም ማሳያ ናቸው።
ይህ ታሪካዊ ዕለት ኢትዮጵያ በአንድ በኩል የታዳሽ ኃይል ሉዓላዊነቷን የምታረጋግጥበትን የአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቱሪዝም ዘርፉንና የባህል እሴቶቻችንን ከፍ የሚያደርገውን የገበታ ለትውልድ አካል የሆነውን የሸበሌ ሪዞርትን ለዓለም ያስተዋወቀችበት አጋጣሚ ነው።
እነዚህ ተግባራት የመደመር እሳቤ ያዋለዳቸው ከሕልም ወደ እውነት የተሸጋገሩ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ምልክቶችና የምሥራቅ አፍሪካ የጋራ ልማት ዋስትናዎች ናቸው።
ዛሬ በሀገራችን እየታየ ያለው ትልቁ ድል ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው መመረቃቸው አይደለም፣ ፕሮጀክት ጀምሮ መጨረስ የዕለት ተዕለት ተግባራችንና መለያችን ሆኗል። ይልቁንም ይበልጥ የሚያስደምመው ሀገሪቱ ከአንድ ግዙፍ ፕሮጀክት ወደ ሌላ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የምትሸጋገርበት ፍጥነት፣ ቅልጥፍ እና የማላቅ አቅም ነው፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬ ታላላቅ ርዕዮችን አልሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር የመለወጥ ብቃት ያለው ትጉህ አመራርና ከእያንዳንዱ የለውጥ ጉዞ ጎን የተሰለፈ ቆራጥ ህዝብ ያላት ሀገር መሆኗን በተግባር አስመስክራለች።
ሰርክ በእያንዳንዱ እለት የሚበሰሩ ውጤቶች፣ ኢትዮጵያ ማንኛውንም ውስብስብ እና ግዙፍ ሥራ የማስተባበርና የመምራት አቅም እንደፈጠረች ማሳያ ናቸው።
የጀመርነውን የመጨረስና የቋጨነውን ደግሞ ለቀጣይ ትውልድ በቅርስነት የማስተላለፍ ባህል በሀገራችን እየተገነባ መምጣቱ ለነገዋ ኢትዮጵያ ታላቅ ተስፋን ሰንቋል።
በእነዚህ ፕሮጀክቶች ምረቃ ላይ የቀጠናችን ሀገራት መሪዎች በጋራ መገኘታቸው ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የምታከናውናቸው የልማት ሥራዎች ሁሉ ከራሷ አልፈው ለጎረቤቶቿ የሚተርፉና ቀጠናውን በጋራ ተጠቃሚነት የሚያስተሳስሩ መሆናቸውን በተግባር አሳይታለች።
የአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የንፋስ ኮሪደር ላይ መገንባቱ፣ ኢትዮጵያ የቀጠናው የታዳሽ ኃይል ማዕከል የመሆን ጉዞዋን የሚያፋጥን ታሪካዊ ክስተት ነው።
ይህ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለሀገራችን ኢንዱስትሪዎች ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጠናው ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስር የጀርባ አጥንት ነው።
በቴክኖሎጂ ለሚመራና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለሚታገዝ ዘመናዊ ኢኮኖሚ ወሳኝ የሆነው ይህ መሰረተ-ልማት፣ በሕዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነት የሚያጠናክር የሰላም ድልድይ ሆኖ ያገለግላል።
ኢትዮጵያ ኃይልን በማመንጨትና ለአጎራባች ሀገራት በማከፋፈል፣ የቀጠናው የኢኮኖሚ ሞተር የመሆን ሚናዋን ቃልን በተግባር በመፈጸም እየተወጣች ትገኛለች።
ሀገራችን ዛሬ ከወንዞቻችን፣ ከንፋስና ከምድር ውስጥ እንፋሎት በምታመነጨው ንጹህ ኃይል በአለም አቀፍ ደረጃ የአረንጓዴ ልማት መሪ እየሆነች መጥታለች።
እነዚህ ስራዎች የኃይል ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ለአለም የበካይ ጋዞችን የመከላከል ጉዞ የበኩሏን ጉልህ አስተዋፅኦ ያሳየችበት አውድ ነው። በተመሳሳይ መልኩ የሸበሌ ሪዞርት ባህላዊ እሴቶቻችንን ከዘመናዊነት ጋር አቀናጅቶ፣ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን ሰፊ አቅም ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የመለወጥ ብቃቷን ያሳየበት የ‘ገበታ ለትውልድ’ ድንቅ ውጤት ነው።
በአጠቃላይ ትላንት በሰላም እጦት ይታወቁ የነበሩ አካባቢዎች ዛሬ የልማት ተምሳሌት መሆናቸው፣ ሀገራችን እየገነባች ያለቸው ሰላም ለልማት ማገር መሆኑን ያረጋግጣል። ኢትዮጵያ የምታልም ብቻ ሳትሆን ሕልሟን ወደ እውነት የምትቀይር፣ የቀጠናውን የልማት ተስፋ የምታለመልምና የአፍሪካ ኩራት ሆና የምትቀጥል ቆራጥ ሀገር ናት።
ትላንት የተመረቁት ፕሮጀክቶች የነገዋን ብልፅግና የምናረጋግጥባቸው ኩሩ ቅርሶቻችን ናቸው። መንግሥት ከቀጠናው ሀገራት ጋር በመሆን ለጋራ ብልፅግና የሚተጋበትን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል።
ህዝባችንም ይህንን የታሪክ እጥፋት በአግባቡ በመረዳትና ለላቀ ሥራ በመነሳሳት የሀገራችንን ከፍታ እንዲያረጋግጥ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ኢትዮጵያ በቀጠናው የብልፅግና ጮራ፣ በአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ሆና መዝለቋን ትቀጥላለች!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!
የኢፌድሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ጥር 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ