የሐሳብ የበላይነትን መሠረት ያደረገ ውድድር ለማካሄድ መዘጋጀታቸውን ፓርቲዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የሐሳብ የበላይነትን መሠረት ያደረገ ውድድር ለማካሄድ መዘጋጀታቸውን ፓርቲዎች ገለጹ
ወልቂጤ፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፡- በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የሐሳብ የበላይነትን መሠረት ያደረገ ውድድር ለማካሄድ መዘጋጀታቸውን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አመራርና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደምስ ገብሬ፤ መጪው ምርጫ የሐሳብ የበላይነት ጎልቶ የሚወጣበት እንዲሆን እንሠራለን ብለዋል።
ፓርቲው በምርጫው የተሻለ ሐሳብ ይዞ በመቅረብና በፖሊሲ አማራጮች ላይ ክርክሮችና ፉክክሮችን በማድረግ የሕዝብ ይሁንታ ለማግኘት በቂ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ለኢዜአ ተናግረዋል።
ለዘላቂ ሰላም፣ ልማትና የሕግ የበላይነት መስፈን በሐሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ አካሄድ መከተል አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ፓርቲው ፍትሐዊ ምርጫ እንዲካሔድ የድርሻውን ከመወጣት ባለፈ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት መጠናከር የሚጠበቅበትን ሚና ይወጣል ብለዋል።
የጉራጌ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባልና በብልጽግና ፓርቲ የጉራጌ ዞን ተወካይ ሔኖክ አብዱልሰመድ በበኩላቸው፤ ምርጫው ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
ምርጫው የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል የሚታይበት እንዲሆንም ፓርቲው ያላሰለ ጥረት እንደሚያደርግ አማላክተዋል።
ፓርቲያቸው የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ሊቀይሩ በሚችሉ ተጨባጭ ጉዳዮች ላይ በማተኮር እንደሚወዳደር ያስታወቁት ደግሞ በእናት ፓርቲ የጉራጌ ዞን አካባቢ ሰብሳቢ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፀሐፊ እንዳለ ኤርጌዶ ናቸው።
የምርጫ ውድድሩ በፖሊሲ አማራጮችና በሐሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን እየሠሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በጋራ ምክር ቤቱ የሚገኙ ሁሉም ፓርቲዎች ለምርጫው ስኬታማነት፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት የበኩላቸውን ለመወጣት እየሠሩ መሆኑም ነው የተገለጸው።