በክልሉ የቤት ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የቤት ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የቤት ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም የሚያስችሉ ተግባራት መጠናከራቸውን የክልሉ የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ አስታወቀ።
በኦሮሚያ ክልል ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ብርሃኑ በቀለ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በክልሉ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ዘርፈ ብዙ እርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው።
በማህበር ማደራጀት፣ የባለሀብቶችን አቅም መጠቀም፣ የዜግነት አገልግሎትና የህብረተሰቡ ተሳትፎ የመኖሪያ ቤት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከሚተገበሩት ተግባራት መካከል መሆኑንም ተናግረዋል።
የመረዳዳት ባህልን በማጎልበት በህብረተሰቡ ተሳትፎ የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤት የማደስና የመገንባት ስራም ውጤት አስገኝቷል ብለዋል።
በግማሽ ዓመቱ 116 ሺህ 429 ቤቶች መገንባት መቻሉን ተናግረዋል።
እንዲሁም በማህበራት ተደራጅተው ቤት ለመገንባት ፈቃድ ከወሰዱት ውስጥ ባለፉት ስድስት ወራት 16 ሺህ 127 ሰዎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን በከተሞቹ የሚስተዋሉትን ህገ-ወጥ ተግባራትን በመከላከልና በመቆጣጠር ላይ በቅንጅት በመስራት ውጤት እየተገኘ ነው ብለዋል ሃላፊው።
ሳይገባቸው የቀበሌ ቤትን በህገወጥ መንገድ የያዙ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ለአብነት በማንሳት፡፡
የአከራይ ተከራይ አዋጅን ተግባራዊ በማድረግ ተከራዮች ላይ ይደርስ የነበረውን ጫና ማቃለል መቻሉን ጠቅሰው ተግባሩ ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው ብለዋል።
ቢሮው ከተሞችን ለነዋሪው ምቹ ለማድረግ፣ አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን፣ ኢንተርፕሩነሮችን ለመፍጠርና የነዋሪውን ኑሮ ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።