ቀጥታ፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያውያን የወል ትርክት ዘካሪ ሐውልት ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፡- የዓድዋ ድል መታሰቢያ ቅድመ አያቶቻችን በኅብር የተቀዳጁትን አኩሪ ድል የሚዘክር የኢትዮጵያውያን የወል ትርክት ዘካሪ ሐውልት ነው ሲሉ ጎብኝዎች ተናገሩ።


 

ከጣሊያን የመጣው ጎብኝ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ኪያ ያደኔ፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ቅድመ አያቶቻችን ለኢትዮጵያ አንድነት የተቀዳጁትን አስደናቂ ገድል የሚዘክር የታሪክ ሐውልት ነው ብሏል።


 

የድል መታሰቢያውም ከኢትዮጵያውያን ባሻገር በመላው ዓለም ለሚኖሩ ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ፋና ወጊና ጥልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ የወል ትርክት መገንቢያ መሳሪያ መሆኑን ለኢዜአ ገልጿል።


 

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ትውልድን የሚያስተምር አስደማሚ ታሪክ የሚዘክር ነው ያሉት ደግሞ ከካሊፎርኒያ የመጡት ሌላኛዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት አዜብ ያደኔ ናቸው።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ቤካ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መታሰቢያው የአሁኑና ቀጣዩ ትውልድ የቅድመ አያቶቹን የድል ታሪክ እንዲገነዘብ በወል ትርክት መገንቢያ መሳሪያነት የሚያገለግል ሕያው ምስክር ነው ብለዋል።


 

በተጨማሪም ለርካታ ጎብኚዎች በመስኅብ መዳረሻነት እያገለገለ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዚህም መሠረት ባለፉት ስድስት ወራት ከ350 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን በማስተናገድ በገጽታ ግንባታና ቱሪዝም ዕድገት ገንቢ ሚና መጫወቱን አስገንዝበዋል።


 

ከጎብኝዎቹ መካከል ከ10 ሺህ የሚልቁት ታዳጊዎች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህም ለአሰባሰቢ ትርክት ግንባታ ዘርፈ ብዙ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ የጋራ ታሪካችን ነጋሪ፣ የነገ ህልማችን ማጠንጠኛና የወል ትርክታችን መሠረት ነውም ብለዋል።


 

የአሁኑ ትውልድም እንደ ዓድዋ ጀግኖች ሁሉ የራሱን ታሪክ በመጻፍ በሀገር ዕድገት የድርሻውን በመወጣት ዐሻራውን ማኖር እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም