ቀጥታ፡

በፕሪሚየር ሊጉ ፋሲል ከነማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል። 

ከቀኑ 10 ሰዓት ፋሲል ከነማ  ከቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

ፋሲል ከነማ በሊጉ ባደረጋቸው 16 ጨዋታዎች በሰባቱ አሸንፎ በአንዱ ተሸንፎ በስምንቱ አቻ ወጥቷል። በ16ቱ ጨዋታዎች 13 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 7 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ፋሲል ከነማ በ29 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። 

ፋሲል ከነማ በዘንድሮው የውድድር ዓመት አነስተኛ ሽንፈት ያስተናገደ እና ዝቅተኛ የግብ መጠን የተቆጠረበት ቡድን ነው። 

ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ 17 ጨዋታዎች አከናውኖ ስድስት ጊዜ ድል ሲቀናው በስድስቱ ተሸንፏል። አምስት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። 15 ግቦችን ሲያስቆጥር 12 ጎሎችን አስተናግዷል።

የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ23 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።

መርሐ-ግብሩ ፋሲል ከነማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣  ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው። 

በሌላኛው መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከነገሌ አርሲ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስከ አሁን በሊጉ ማሸነፍ የቻለው ጨዋታ ብዛት አራት ብቻ ነው። አምስት ጊዜ ሲሸነፍ ስምንት ጊዜ አቻ ወጥቷል። 20 ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ 20 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ20 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ተጋጣሚው ነገሌ አርሲ በበኩሉ 17 ጨዋታዎችን አድርጎ ስምንት ጊዜ ሲያሸንፍ አራት ጊዜ ተሸንፏል። በአምስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 18 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 12 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

ነገሌ አርሲ በ29 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። 

በ17ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮጵያ ቡናን፣ ነገሌ አርሲ የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።  

ሁለቱም ቡድኖች በድል ጉዞ ለመቀጠል የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።  

ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ መቀሌ 70 እንደርታ ከኢትዮጵያ ቡና በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

መቀሌ 70 እንደርታ በ17 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ኢትዮጵያ ቡና በ19 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። 

በ17ኛ ሳምንት መቀሌ 70 እንደርታ ከአዳማ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል። ኢትዮጵያ ቡና ባለፉት ሶስት የሊጉ ጨዋታዎች አላሸነፈም። 

ጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው። 

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ16 ነጥብ 19ኛ እና አርባምንጭ ከተማ በስምንት ነጥብ 20ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

ወልዋሎ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል። በሊጉ እስከ አሁን ምንም ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻለው ብቸኛው ክለብ አርባምንጭ ከተማ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት ይጫወታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም