ኢትዮጵያ የሥራ እና የተጨባጭ ውጤት ምድር እየሆነች ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የሥራ እና የተጨባጭ ውጤት ምድር እየሆነች ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ዛሬ የተስፋ ብቻ ሳይሆን የሥራ እና የተጨባጭ ውጤት ምድር እየሆነች ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
አቶ ተመስገን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ከ’ገበታ ለትውልድ’ ዐቢይ ፕሮጀክቶች መካከል ሁለተኛው እና በ385 ሔክታር ላይ ያረፈው የሸበሌ ሪዞርት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሪዞርቱ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በተያዘው ጉዞ ላይ ትልቅ እጥፋትን የሚፈጥር ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሐሳብ ዘር እስከሚታይ ውጤት በሚመነዘሩ የትጋት ልኬቶች የተጀመሩት የ“ገበታ” ፕሮጀክቶች፣ የሀገራችንን እምቅ ፀጋዎች ለዓለም ገበያ እያወጡ ይገኛሉ ብለዋል።
በመደመር እሳቤ እየተገነቡ የሚገኙት እነዚህ ፕሮጀክቶች ያለንን ዐቅም በማቀናጀት፣ ለላቀ ውጤትና ከፍታ እንድንጓዝ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን።
የሸበሌ ሪዞርት የሶማሌ ክልልን የሀገራዊ ልማት ኢኒሼቲቭ ትሩፋቶች ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ፣ የምስራቅ ኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ትልቅ ዐቅም መሆኑንም አስታውቀዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ ዛሬ የተስፋ ብቻ ሳይሆን የሥራ እና የተጨባጭ ውጤት ምድር እየሆነች ነው ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል።