የኦሮሚያ ክልል ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተሰራው ስራ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ ክልል ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተሰራው ስራ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል
አዳማ፤ ጥር 23/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ የተሰራው ስራ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ ገለጹ።
አዳማ የስምጥ ሸለቆ የቱሪስት ከተማ መሆኗን ለማስተዋወቅ ያለመ የከተማዋ ነዋሪዎች የተሳተፉበት የምሽት የታላቁ ሩጫ ውድድው ተካሄዷል።
በሩጫው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ በክልሉ የተከናወኑ የከተሞች ልማት ስራዎች ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ አስችሏል ብለዋል።
በተለይም በክልሉ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ ከተሞችን ተመራጭ የቱሪስት መደረሻ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ማዕከል እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተሞች ውብ፣ ጽዱ እና ምቹ እየሆኑ መምጣታቸው የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ለመለወጥ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ረገድ በጎ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
አዳማ በተሻለ መልኩ የከተማ ልማት ስራዎች ከተከናወነባቸው ከተሞች መካከል አንዷ መሆኗን ጠቅሰው ከተማዋ ወደ ዘመናዊ ከተማነት እየተሸጋገረች መሆኑንም አስረድተዋል።
በዚሁ መነሻነት ለመጀመሪያ ጊዜ የከተሞችን የኮሪደር ልማት ለማስተዋወቅና የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግ ያለመ የምሽት የሩጫ መርሃ ግብር ዛሬ መካሄዱን ተናግረዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው የአዳማ ከተማን ለነዋሪቿ ምቹ ለማድረግ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ማእከል እንድትሆን በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በቀጣይም ከተለመደው መንገድ በመውጣትና ሌት ከቀን በመስራት የከተማዋን ዘመናዊነት እና እድገት የሚያፋጥኑ ስራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል።
በከተማዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎችን ለማሳካት ፍጥነትና ጥራት ወሳኝ ነው ያሉት አቶ ሃይሉ ለዚህም ህዝቡ የጀመረውን ድጋፍ ማጠናከር አለበት ብለዋል።
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ነጋ ወዳጆ በበኩላቸው ቱሪዝም የከተሞችን እድገት ከማፋጠን ባለፈ አንድነት እና ህብረትን ያጠናክራል ብለዋል።
ዛሬ በአዳማ ከተማ የተካሄደው የምሸት ሩጫ ከተማዋን የበለጠ በማስተዋወቅ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን የላቀ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ፣ የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ፣ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ቢያንን ጨምሮ ሌሎች የክልሉና የከተማ መስተደድሩ አመራሮችና የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።