የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ የቱሪዝም አቅም በመጠቀም ሀገሪቷን የዘርፉ የስበት ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ የቱሪዝም አቅም በመጠቀም ሀገሪቷን የዘርፉ የስበት ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
ሀዋሳ ፤ጥር 23/2018 (ኢዜአ) :- የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ የቱሪዝም አቅም በመጠቀም ሀገሪቷን የዘርፉ የስበት ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸው ተመላከተ።
የቱሪዝም ሚኒስቴር የኢትዮጵያን ቡና ለቱሪዝም መዳረሻነት ለማዋል የሚያስችሉ ስራዎችን ለማጠናከር ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የቡና ቱሪዝም ሴሚናርና የመስክ ምልከታ በሲዳማ ክልል ተካሄዷል።
በሚኒስቴሩ የቱሪዝም መስህብ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሳ ከድር እንደገለጹት የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ የቱሪዝም አቅም በመጠቀም ሀገሪቷን የዘርፉ የስበት ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል።
የተጀመሩ ትልልቅ የቱሪዝም ስራዎችን ለማጠናከር የፖሊሲ አቅጣጫ፣ የተቀናጀ ትብብርና ስልት ተነድፎ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አውስተው እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን ለማስቀጠል ያሉ ሀብቶችን የመለየትና የመጠቀም ስራ ይሰራል ብለዋል።
እንዲሁም አዳዲስ ያልተዳሰሱ ዘርፎችና ዕምቅ አቅሞች የመለየት ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተው ከዚህ ውስጥ አንዱ ቡናን በተለየ አቀራረብ ለቱሪዝም መዳረሻነት ለማዋል የሚያስችል ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
የቡና መገኛ በመሆናችን ከባህልና ታሪክ ጋር ያለንን ማህበረሰባዊ ትስስር እንዲሁም የምርት ሂደቱ ከእርሻ እስከ ቅምሻ ድረስ ያለውን ሂደት በተቀናጀ መንገድ ለቱሪዝም መዳረሻነት ለማዋል በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የቱሪስት መስህብና መዳረሻ ልማት ዳይሬክተር አቶ ካሳ መንገሻ በበኩላቸው የክልሉ የቡና ልማት ለቱሪዝም መዳረሻነት አማራጭ አቅም መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል የመፍጠርና የቱሪዝም ገቢን የማጠናከር ዕድል ይዞ የሚመጣ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም እንደ ክልል አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከግብርናና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራን ነው ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬቴርስ አሶሲዬሽን የመጣችው ቅድስት ሀይሉ የቡና አብቃይ አካባቢዎችን ለቱሪዝም መዳረሻነት ለማዋል የተጀመረው ስራ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሳለች።
ቡናን ከቱሪዝም ጋር ማቆራኘቱ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሳድገው የገለፁት ደግሞ በሲዳማ ክልል ወንሾ ወረዳ በቡና ልማት ላይ የተሰማራ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ሰብሳቢ አቶ አድማሱ አደም ናቸው።
ምቹና ጽዱ አካባቢን በመፍጠር ጎብኚዎችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንም አክለዋል።