ቀጥታ፡

የአይሻ-2 ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ንግድና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት በዜጎች ህይወት ላይ ቀጥተኛ ፋይዳ አለው

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018(ኢዜአ)፦ የአይሻ-2 ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ንግድና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት በዜጎች ህይወት ላይ ቀጥተኛ ፋይዳ እንዳለው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌ፣ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በተገኙበት የአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

በሶማሌ ክልል የተገነባው የአይሻ-2 ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 120 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 80 ሜጋ ዋት ማምረት የሚችለው ምእራፍ በዛሬው እለት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።


 

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ኢትዮጵያ የፈጠረችው የኃይል አቅርቦት አቅም የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው።

ይህም የኢንዱስትሪ ሽግግርና የተለያዩ አገልግሎቶችን በማሳለጥ በሀገር ዕድገት ላይ እመርታዊ ውጤት እንዲመዘገብ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ግንባታ በታዳሽ ኃይል የተመሰረተ መሆኑም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመቀነስ ለዘላቂ የአካባቢ ደኅንነት ወሳኝ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የአይሻ-2 የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትም ሁሉን አቀፍ ዕቅድ አካቶ የተገነባ ሀገር አቀፍ የልማት ስኬት መሆኑን አንስተዋል።

የፕሮጀክቱ ለስኬት መብቃትም የኃይል አቅርቦት አቅምን በማጎልበት ህብረተሰቡ አስተማማኝና ወጥ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኝ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።

በቀጣይም ጤና፣ ትምህርት፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ለዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ቀጥተኛ ትርጉም እንደሚያመጣ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም