ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከባህርዳር ከተማ ጋር አቻ ተለያየ 

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ሲዳማ ቡና እና ባህርዳር ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል። 

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም መስፍን ታፈሰ በ61ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ሲዳማ ቡና መሪ ሆኗል።

ከእረፍት መልስ ሰቲህ ኦሴ በ71ኛው ደቂቃ የባህር ዳር ከተማን የአቻነት ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል። 

ውጤቱን ተከትሎ የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ነጥቡን ወደ 34 ከፍ አድርጓል። ከተከታዩ ሀዋሳ ከተማ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ከአራት ወደ ሁለት ዝቅ ብሏል። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አላሸነፈም።

ባህርዳር ከተማ በ22 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባህርዳር ከተማ ለ11ኛ ጊዜ አቻ በመውጣት በሊጉ በበርካታ ጨዋታዎች አቻ የወጣ ቡድን ሆኗል። 

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው መርሐ-ግብር ሸገር ከተማ መቻልን 1 ለ 0 አሸንፏል።

ቡልቻ ሹራ በ59ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።

ከስምንት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ሸገር ከተማ በ20 ነጥብ ደረጃውን ከ16ኛ ወደ 13 ከፍ አድርጓል። በሊጉ አራተኛ ድሉን አስመዝግቧል።

ከሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ሽንፈት ያስተናገደው መቻል በ29 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። በውድድር ዓመቱ ያስተናገደው ሽንፈት ብዛት አምስት ደርሷል።

ቀን ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን 2 ለ 0 አሸንፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም