ቀጥታ፡

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የኃይል አማራጭ ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የኃይል አማራጭ ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌ፣ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በተገኙበት የአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

በሶማሌ ክልል የተገነባው የአይሻ-2 ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 120 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 80 ሜጋ ዋት ማምረት የሚችለው ምእራፍ በዛሬው እለት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።


 

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ በዚሁ ወቅት፤ የኃይል አቅርቦት ደኅንነት፣ የሀገርን ልማትና ዕድገት ማፋጠን መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን የዕድገት ጉዞ የሚያፋጥን የኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማት የማጎልበት ሥራ በትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በነፋስ፣ በፀሐይና ሌሎች የኃይል አማራጮች የተገነቡ የመሠረተ ልማት ስኬቶች ዕድገትን በማፋጠን አዎንታዊ ሚና እየተወጡ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሕዳሴ ግድብና ሌሎች የኃይል አማራጭ የታዳሽ ኃይል መሠረተ ልማት ስኬቶችም ኢትዮጵያን የኃይል ማዕከል እንዳደረጓት አብራርተዋል።

በዚህም ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካ ምርጡ የኃይል ፕሮጀክት በሚል ኢትዮጵያን በአፍሪካ ንግድ ቻምበር ዕውቅና እና ሽልማት እንዳስቸራትም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የመፈጸም አቅሙን ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት እያሳደገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም ለኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት ተደራሽነትና አቅም ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን በማስጠበቅ የዜጎችን የኃይል አቅርቦት ፋላጎት ለማሟላት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም